በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የኮቪድ-19 መከላከያ ቁሳቁሶችን በሀገር ውስጥ በማምረት 66 ሚሊዮን ዶላር ማዳን ተችሏል


ነሀሴ 14/2013 (ዋልታ) – በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የኢንዱስትሪ ፓርኮች የኮቪድ-19 መከላከያ ቁሳቁሶችን እንዲያመርቱ በማድረግ 66 ሚሊዮን ዶላር ማዳን መቻሉን የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታውቋል።
በኮርፖሬሽኑ የዋና ስራ አስፈጻሚ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዲሱ ማሞ የ2013 ዓ.ም በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸምን አስመልክተው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
ኃላፊው በዚህን ወቅት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የኢንዱስትሪ ፓርኮች የኮቪድ-19 መከላከያ ቁሳቁሶችን በስፋት ማምረት መቻላቸውን ገልጸዋል።
በተለይ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ማስክ እንዲሁም ለህክምና ባለሙያዎች የሚውል የኮሮናቫይረስ መከላከያ ቁሳቁሶችን በስፋት ማምረታቸውን ተናግረዋል።
“በዚህም ቁሳቁሶቹን ከውጭ ለማስገባት ይወጣ የነበረውን 66 ሚሊዮን ዶላር ማዳን ተችሏል” ብለዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ኮርፖሬሽኑ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች 400 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ለማግኘት አቅዶ፤ 247 ሚሊዮን 900 ሺህ ዶላር ገቢ መገኘቱን ገልጸዋል።
ይህም የእቅዱን 54 በመቶ ብቻ ማሳካት መቻሉን እንደሚያመላክት ጠቅሰው፤ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ተጽእኖ ለአፈጻጸሙ መቀነስ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል።
ኮርፖሬሽኑ በተያዘው በጀት ዓመት የባህርዳር፣ የድሬዳዋና የሠመራ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ወደ ስራ በማስገባት በሀገር አቀፍ ደረጃ ያሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ቁጥር ወደ 13 ከፍ ማድረጉንም ነው የገለጹት።
በሚቀጥሉት 20 ዓመታት በኢትዮጵያ 107 የኢንዱስትሪ ፓርኮችን የመገንባት እቅድ መያዙን ጠቅሰው፤ ፓርኮቹ የሚገነቡባቸው ሁኔታዎችን በሚመለከት ከወዲሁ ጥናት መጀመሩን አብራርተዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።