ሰኔ 2/2013 (ዋልታ) – በትግራይ ክልል የመልሶ ማቋቋም ሂደት በጤናው ዘርፍ 52 ከመቶ ሆስፒታሎች መደበኛ ስራ መጀመራቸውን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ የክልሉ ማህበረሰብ የጤና ዘርፍ ላይ የተከናወኑ ስራዎችን አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።
መግለጫውን የሰጡት የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በሚኒስቴሩ ደረጃ የተቋቋመው የድጋፍ ግብረሃይል ከክልሉ ጤና ቢሮ ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ ቅድሚያ ተሰጥቶት ወደ ተግባር የተገባው የጤና አቅርቦቶችን አገልግሎት ማስጀመር ነው ብለዋል።
በዚህም ባለፈው ሳምንት ከነበረው ሪፖርት አኳያ አሁን ላይ በክልሉ 55 ከመቶ ሆስፒታሎች እና 52 ከመቶ የጤና ማዕከላት ስራ እንዲጀምሩ ተደርጓል።
ዶ/ር ሊያ ታደሰ አገልግሎት በተጀመረባቸው የጤና ፋሲሊዎች 85 ከመቶ በላይ የጤና ባለሞያዎች የእለት ተለት ስራቸውን በማከናወን ላይ ይገኛሉ ብለዋል።
በተቀሩት የጤና ተቋማት ላይ የደረሰው ጉዳት መገምገሙን ገልጸው፤ለዚህም የፌዴራል መንግስት ባቀረበው በጀት በ14 ሆስፒታሎች እና 58 የጤና ማዕከላት አገልግሎት እንዲጀመር ይደረጋል ነው ያሉት።
በሌላ በኩል በክልሉ አስፈላጊውን የቁሳቁስ አቅርቦት ማድረስ ነው ያሉት ዶ/ር ሊያ በዚህም ለ40 የጤና ማዕከላት ኪትስ ተልኳል።
የጤና ቁሳቁስ ከተላከባቸው አካባቢዎች መካከል መቀሌ፤ ኩይሃ ፤አቢ አዲ፤እና ሽሬ ይገኙበታል።
የክልሉን የጤና አገልግሎት ለማስጀመር በሚደረገው ጥረት እስካሁን 310 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ የሚያወጣ መድሃኒት እና የህክምና መሳሪያ ወደ ክልሉ መላኩን ሚኒስትሯ ገልጸዋል።
የትግራይ ክልል ጤና መልሶ መቋቋም እንቅስቃሴ ምላሽ በማገዝ ሂደት የጤና ሚኒስቴርም ከአጋር አካላት ጋር በመሆን 215 በላይ ሚሊዮን ብር የሚገመት ገንዘብ ለክልሉ ተላልፏል።
የጤና አገልግሎት ባልተጀመረባቸው አካባቢዎችም ተንቀሳቃሽ ቡድኖችን በመጠቀም ህብረተሰቡን ተደራሽ የማድረግ ስራ በመከናወን ላይ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።