በትግራይ ክልል 400 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ መግባቱ ተገለጸ

ግንቦት 03/2013 (ዋልታ) – በትግራይ ክልል በ2013/14 ምርት ዘመን መኸር ወቅት ከሚያስፈልገው የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ ግማሽ ያህሉ ወደ ክልሉ መድረሱን የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የእርሻና ገጠር ልማት ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ብርሀነ አርዓያ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በምርት ዘመኑ የመኸር ወቅት ክልሉ 800 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ ያስፈልገዋል።
ከዚህ ውስጥ 400 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ ወደ ክልሉ መድረሱን ገልጸዋል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ ለክልሉ የማዳበርያ መግዥያ በሰጠው የ1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር የብድር ዋስትና መሰረት ማዳበሪያው እየቀረበ መሆኑን ምክትል የቢሮ ሃላፊው አስታውቀዋል።
ማዳበሪያን ለአርሶ አደሩ ለማሰራጨት ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነም አመልክተዋል።
የህብረት ስራ ማህበራት መጋዘኖቻቸውን የማዘጋጀትና የአርሶ አደሩን የማዳበሪያ ፍላጎት የመለየት ስራዎች መከናወናቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።
በየወረዳው የሚገኙ የእርሻና ገጠር ልማት መዋቅሮችን ዳግም የማደራጀት ስራም መካሄዱን ጠቁመዋል።
በዚህ ሳምንት ውስጥ ማዳበርያውን ወደ ወረዳዎች የማጎጎዝ ስራ እንደሚጀመር አመላክተዋል።
ከዚሁ ጎን ለጎን ለምርት ወቅቱ ከሚያስፈልገው ከ400 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ውስጥ የ150ሺህ ኩንታል ግዥ ተፈጽሞ ወደ ክልሉ እየተጓጓዘ መሆኑን ተናግረዋል።
የምርጥ ዘር ግዥው በፌደራል መንግስትና በሌሎች አካላት መፈጸሙን ኃላፊው አስታውቀዋል።