በትግራይ ክልል ሲካሄድ የቆየው ህግ የማስከበር ስራው በከሀዲው ጁንታ ላይ ብቻ ያነጣጠረ ነው- ዶ/ር አለሙ ስሜ

በትግራይ ክልል ሲካሄድ የቆየው ህግ የማስከበር ስራው በከሀዲው የህወሓት ጁንታ ቡድን ላይ ብቻ ያነጣጠረ እንጂ ንፁሓን የትግራይን ህዝብ አለመሆኑን የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽ/ቤት የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሲቪል ማህበራት ዘርፍ ሃላፊ ዶ/ር አለሙ ስሜ ገለጹ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ከሚኖሩ የትግራይ ተወላጅ ወጣቶች ጋር በተካሄደው መድረክ የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽ/ቤት የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሲቪል ማህበራት ዘርፍ ሃላፊ ዶክተር አለሙ ስሜን ጨምሮ የሴቶች፣ ወጣቶችና ህጻናት ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ አልማዝ እና በአዲስ አበባ ብልፅግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ አዕምሮ አዱኛ በመገኘት ለወጣቶቹ መልእክት አስተላልፈዋል።

ዶ/ር አለሙ በውይይት መድረኩ ማጠቃለያ እንደ አገር ለውጥ ውስጥ መኖራችንን እና የለውጡ ፈተና ዋነኛው ሕወሓት ውስጥ የመሸጉ ጁንታ እንደነበረ አስታውሰዋል።

ለውጡ ማንንም የሚጎዳ ሆኖ ሳይሆን አገር መዝረፊያ መንገዶች ይዘጉብኛል፤ የበላይና አድራጊ ፈጣሪ ሆኖ የመቀጠል መንገድን ይዘጋብኛል ብሎ ስለሰጋ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

እንደ እሳቸው ገለጻ “ይህን ለውጥ ለመቀልበስ ካልሆነ ደግሞ አገሪቱን ለማፍረስ የሚሰሩትን ክፉ ስራና ሴራ እየታወቀ ህዝቡ ክፋታቸው የገባው እለት እራሱ ያስወግዳቸዋል፤ ለጥቂት ሴረኞች ተብሎ የትግራይ ህዝብ ቀየ ላይ እሳት መንደድ የለበትም ብለን ታግዘን ሳለን ነው የአገር አለኝታ የሆነው የመከላከያ ሠራዊት ላይ ቃታ ስበዋል፤ የክህደትና ወንባዴነቱን ጥግ አሳይቶናል” ብለዋል።

በዚህ መልኩ ተገደን የገባንበትን የህግ ማስከበሩ ዘመቻ በአመራሩና በመከላከያ ሠራዊቱ ጥበብ ምክንያት ህዝቡ ላይ የጎላ ጉዳት ሳይደርስ  በቀላል ዋጋ መወጣት ችለናል ብለዋል።

አሁን ትኩረቱ አገርና ክልሉን መልሶ መገንባት ላይ ነውም ብለዋል።

የሽንፈቱ መንስኤም ከህዝብ ጋር መጣላቱ ነው፤ የትግራይ ህዝብ ጨምሮ የሁሉንም ህዝብ ድጋፍ ስለ አጣ ነው፤ ይህ እነሱ አሸነፍን ብሎ ለሚፎክሩ ደርግንም የጣለ ይህ ነው ብለዋል።

ወጣቱ ከዚህ ቡድን ውድቀት በተለይ ከጁንታው ቡድን እበሪትና ከእኔ በላይ ማን አለ መማር አለበት፤ በዚህ ድል ከልክ በላይ መደሰትና መፎከርም አያስፈልግም፤ የድል ማግስትን ሁኔታ በአግባቡ መያዝ አለብን ሲሉም አሳስበዋል።

“ይህ ቡድንና የክፋት አካሄዱ ዛሬ የለም ታሪክ ሆነዋል”፤  ያሉት ሃላፊው ኢትዮጵያ ችግር ግን እርሱ ብቻ አይደለም ድህንነት የሚባል ከባድ ፈተና አለብን ያሉት ዶክተሩ በጋራ መቆም እንደሚገባ አሳስበዋል።

በጋራ መስራትና በአንድነት መቆምም እንዳንችል የተሰራው ስራ የተረጨው መርዝ ብዙ ነው ያሉት ሃላፊው በጋራ እንዳንቆም የተሰራውን ስራ በብልሃት መሻገር የጋራ ጠላታችን ላይ መነሳት አለብን።

ወንድማማችነታችን ማጠናከር አለብን ይህን ደግሞ ከፊት ሆኖ መምራት ያለበት ወጣቱ ነው ብለዋል።

ጁንታው የሰራው ስራ የሚያመጣው የስነ ልቦና ጫና ህዝቡን እንዳይጎዳ፤ ሁሉም ንጹህ ህዝብና ጁንታውን መለየት ለዚህ ህዝብ ስነልቦና መጠንቀቅ አለበት።

በክልሉ ለውጡን መሬት ለማስነካትና ልማትና ዴሞክራሲን ለማረጋገጥ ወጣቱ ከፊት መሰለፍ አለበት፤ ሚናውም የሚተካ አይደለም ብለዋል ዶ/ር አለሙ በመልእክታቸው።

ወይዘሮ አልማዝ በበኩላቸው ወጣቶች በአገርና መኖሪያ አካባቢ ለውጥ ለማምጣትና አዲስ መንገድ ለመጀመር  ወሳኞች በመሆናቸው፤ የትግራይ ተወላጅ ወጣቶችም  በትግራይ ክልል እንዲመጣ የሚፈለገውን ለውጥ ከፊት ሆኖ መምራት ይገባቸዋል ማለታቸውን ፓርቲው አስታውቋል።