በትግራይ ክልል በ9 ወራት 227 አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ ገቡ

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል

ግንቦት 14/2016 (አዲስ ዋልታ) በትግራይ ክልል ባለፉት ዘጠኝ ወራት 227 አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ መግባታቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለጹ፡፡

በኢንድስትሪ፣ ማዕድንና አምራች ዘርፉ ባለፉት 9 ወራት 176 ሺሕ በላይ አዳዲስ የሥራ ዕድሎች መፈጠራቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርቶች በመተካት እና ወጪ ንግድን በመደገፍ የውጪ ምንዛሬ ማዳን መቻሉን ተናግረዋል፡፡

3 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ግምት ያላቸው 2 ነጥብ 2 ሜትሪክ ቶን ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት መቻሉን ጠቁመው በዚህም 1 ነጥብ 9 ቢሊየን ዶላር ማዳን መቻሉን አንስተዋል፡፡

10 ነጥብ 5 ሜትሪክ ቶን የኢንዱስትሪ ግብዓት አቅርቦት በማቅረብ የጨርቃ ጨርቅ፣ ምግብና ብረታ ብረት፣ የቆዳና ሌጦ ኢንዱስትሪዎች ተጠቃሚ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

107 ሺሕ ቶን ምርቶች ወደ ውጪ ሀገራት ተልከው 202 ሚሊየን ዶላር እንደተገኘም ሚኒስትሩ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኢንዱስትሪና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረቡት ሪፖርት ተናግረዋል፡፡

20 ቢሊየን ብር ግምት ያለው የውጪ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብ እንተቻለም ገልጸዋል።

ክልሎች ሰላምና ጸጥታን በማስጠበቅ ራሳቸውን ለኢንቨስትመንት ምቹ ማድረግ የኢንቨስትመንት ፍሰቱን ማሳደግ እንደሚገባቸውም አጽንኦት መስጠታቸውን የምክር ቤቱ መረጃ ያመላክታል፡፡

በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የምርትና የግብዓትና የገበያ ትስስር ለመፍጠር በጎ ተፅዕኖ ማሳደሩም ተመልክቷል።

በሚኒስቴሩ የ9 ወራት አፈፃፀም የተስተዋሉ ጠንካራና ደካማ ጎኖች በቋሚ ኮሚቴው ቀርበው ምላሽ እየተሰጠባቸው ይገኛል።