በትግራይ ክልል ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ ተማሪዎች በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ

ሰኔ 24/2013(ዋልታ) – በትግራይ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የሚማሩ ተማሪዎች በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ ሲል የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

በትግራይ ክልል ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች የሚማሩ ተማሪዎችን በተመለከተ ተቋሙ ከተለያዩ አካላት፣ የዩኒቨርስቲዎቹ አመራሮች እና ከዓለም አቀፍ ተራድኦ ተቋማት ጋር በመሆን ጉዳዩን እየሰራበት ይገኛል፡፡
በተደረገው ጥረትም የዩኒቨርቲዎችን አመራር ለማግኘት የተቻለ ሲሆን ተማሪዎች በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኙና የሁለተኛ መንፈቅ ዓመት ፈተና ለመውሰድ በዝግጅት ላይ ያሉም እንዳሉ አስታውቋል፡፡
የተማሪ ወላጆች ልጆቻቸው በመልካም ሁኔታ ላይ መሆናቸውን ተረድተው በመንግስት የተጀመሩ ጥረቶችን እንዲደግፉ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ተማሪዎች ፈተና ወስደው ሲጨርሱ የሚኖሩ ጉዳዮችን የምናሳውቅ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ የተማሪ ወላጆች በመደበኛ መገናኛ ብዙኃን የሚተላለፉ መረጃዎችን ብቻ እንዲጠቀሙ እና ተረጋግተው እንዲጠብቁ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አሳስቧል።