በትግራይ ክልል አገልግሎት መስጠት አቁመው የነበሩ ጤና ተቋማት አገልግሎት መስጠት እየጀመሩ ነው – የጤና ሚኒስቴር

            የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ

የካቲት 04/2013 (ዋልታ) – በትግራይ ክልል በከፊል እና ሙሉ በሙሉ አገልግሎት መስጠት አቁመው የነበሩ ጤና ተቋማት አገልግሎት መስጠት እየጀመሩ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ አስታውቀዋል፡፡

ሚኒስትሯ የጤና ተቋማቱን ወደ አገልግሎት ለመመለስ የጤና ሚንስቴር፣ የትግራይ ክልል ጤና ቢሮ ከአጋር ድርጅቶች እና ሌሎች መንግስታዊ ተቋማት ጋር በመሆን ድጋፍ እና ክትትል እያደረጉ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡

ተቋማቱን ወደ አገልግሎት ለመመለስ የሚያስችሉ መድሀኒቶችን እና የሕክምና መገልገያዎችን የሚያሰራጩ የመቐሌ እና የሽሬ የመድሀኒት አቅርቦት ቅርንጫፎች በሙሉ አቅማቸው እየሰሩ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡

በክልሉ ተቋማቱ አገልግሎት መስጠት ሲጀምሩ የደም አቅርቦት እጥረት እንዳያጋጥም በክልሉ የሚገኙ የደም ባንኮች ወደ ስራ እንዲገቡ የተደረገ መሆኑን የጠቀሱት ደ/ር ሊያ፣ በነዚህ ባንኮች ለማይሸፈኑ ፍላጎቶች ከማዕከል ደም እየተላከ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እስካሁን በተደረገው ድጋፍ እና ክትትል የመድሀኒትና ግብአት ስርጭት ተደርጎ ወደ ስራ የገቡ ጤና ተቋማት ቁጥር 88 መድረሱንም አረጋግጠዋል፡፡

በዚህም በክልሉ አምስት ዞኖች ካሉት 40 ሆስፒታሎች መካከል 15 ሆስፒታሎች ሙሉ በሙሉ እና 5 ሆስፒታሎች በከፊል አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡

በአምስቱ ዞኖች መካከል ካሉት 224 ጤና ጣቢያዎች መካከል ደግሞ 68ቱ አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውንም አመልክተዋል፡፡

ቀሪዎቹን ሆስፒታሎች እና ጤና ጣቢያዎችን በአጭር ጊዜ ወደ አገልግሎት ለመመለስ እና የጤና አገልግሎቶችን ለሕዝቡ ተደራሽ ለማድረግ የጤና ሚንስቴር፣ ኤጀንሲዎች እና የክልሉ ጤና ቢሮ ከአጋር ድርጅቶች ጋር በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን ዶ/ር ሊያ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው አስታውቀዋል፡፡