በትግራይ ክልል ጭላ ወረዳ በአንድ አካባቢ ጁንታው ደብቋቸው የነበሩ ከ140 በላይ ከባድና ቀላል ተሽከርካሪዎች ከጦር መሳሪያ ጋር ተገኙ

በትግራይ ክልል ማእካላዊ ዞን የጭላ ወረዳ በአንድ አካባቢ ጁንታው ደብቋቸው የነበሩ ከ140 በላይ ከባድና ቀላል ተሽከርካሪዎችና የተለያዩ ፈንጅዎች ጨምሮ በርካታ የከባድ መሳሪያ ተተኳሾች ሰራዊቱ ባደረገው አሰሳ  አግኝቷል።

በአካባቢው የተሰማራው የ11ኛ ክፍለ ጦር 3ኛ ብርጌድ አዛዥ ኮሎኔል ያሲን ኑርዬ እንደገለፁት፣ የህወሓት ጁንታ “ሰራዊቱ አይደርስበትም” ብሎ ባሰበው የጭላ ወረዳ ልዩ ስፍራው ሰረፍረፍ በተባለ አካባቢ ስንቅና ትጥቅ የጫኑ በርካታ ተሽከርካሪዎችን ደብቋቸው  ተገኝተዋል።

በአካባቢው የተሰማራው ሰራዊት ባደረገው ህግን የማስከበር ተግባር እና አሰሳ  የተደበቁት መኪኖች ፣ቀላል እና ከባድ  የጦር  መሳሪያዎች ጭምር መገኘታቸውን ኮሎኔል ያሲን ተናግረዋል።

የ11ኛ ክፍለ ጦር 1ኛ ብርጌድ አዛዥ ኮሎኔል ያረጋል መኮንን በበኩላቸው ፣ አካባቢው ከጁንታው አባላት ሙሉ ሙሉ ነፃ በመውጣቱ ህብረተሰቡ ወደቀደመ የተረጋጋ ህይወቱ እየተመለሰ እንደሚገኝና ሰራዊቱ የህብረተሰቡን ሰላም ከማስጠበቅ አንፃር በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ መግለጻቸውን ከኢፌዴሪ  መከላከያ ሠራዊት ያገኘነው  መረጃ  ያመለክታል።