በትግራይ የተካሄደው ሕግ የማስከበር ዘመቻ የሕዝቦችን ደህንነት እና የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር የተወሰደ ነው – አምባሳደር ማይክል ሬይነር

በትግራይ የተካሄደው ሕግ የማስከበር ዘመቻ መንግሥት የሕዝቦችን ደህንነት እና የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር ያለበት ኃላፊነትን ለመወጣት የወሰደው መሆኑን ተሰናባቹ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክል ሬይነር አስታወቁ።
መንግሥት የሕዝብን ደህንነት እና የሀገር ሉዓላዋነትን የማስከበር ኃላፊነት አለበት ያሉት አምባሳደሩ፣ ከዚህ አንጻር የወሰደው እርምጃ ተገቢ እና በአሜሪካ መንግሥት ተቀባይነት ያለው እንደሆነ አስታውቀዋል።
ማንኛውም መንግሥት በትጥቅ ከተደገፈ አመፅ ራሱን የመከላከል መብት እና ግዴታ አለበት፤ እኔ እና እኔ የምወክለው መንግሥት ትኩረት አሁን ባለው የጦርነቱ ማግስት ሁኔታ ላይ ነው ብለዋል።
መንግሥታቸው በጦርነቱ የተሳተፉትን ሁለቱን አካላት በእኩል ደረጃ እንደማያይ ከመጀመሪያው ግልጽ አድርገናል ያሉት አምባሳደር ሬይረር፣ አንደኛው የሀገሩን የግዛት አንድነት እና የሕዝቦቹን ደህንነት የመጠበቅ ግዴታ ያለበት የፌዴራል መንግሥት፣ ሌላናው ደግሞ በሕገወጥ የትጥቅ አመፅ የተሳተፈ እንደሆነ አስታውቀዋል።
ይህም ሆኖ ጦርነት ምንግዜም ጥሩ ውጤት እንደሌለው፣ የጦርነት ማግስት ሁሌም የጠራ ሆኖ እንደማያውቅ፣ ምንጊዜም የተመሰቃቀለ እንደሆነ አስታውቀዋል።
አሁን ያለነው በዛ ወቅት ላይ በመሆኑ ትኩረታችንም እሱ ነው ብለዋል።
በአካባቢው የተራዘመ የሰብአዊ አቅርቦት ፍላጎት መኖሩንም ጠቁመው፣ ኢትዮጵያውያን ሆኑ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያርጉ የበለጠ ሥራ መሠራት አንዳለበትም አመልክተዋል።
አምባሳደሩ ከሦስት ዓመት በበለጠው የኢትዮጵያ ቆይታቸው፤ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ስለክብር፣ ጀግንነት፣ ራስን መቻል፣ እምነት፣ ጽናት፣ ቆራጥነት፣ ደስታ፣ ኅብረት እና አንድነት በብዙ ተምሬያለሁ ብለዋል።
“ድንቅ አገራችሁን፣ ውብ ባሕላችሁን እና ጠንካራ መንፈሳችሁን ስላሳወቃችሁን እና ስላጋራችሁን እናመሰግናለን! ላካፈላችሁኝ ልምድ እና ጥበብ ዘለዓለማዊ ባለውለታዬ ናችሁ! ለእያንዳንዳችሁና ለታላቋ አገራችሁ ሰላም፣ ጤና እና ደስታን እመኝላችኋለሁ” ብለዋል።
ኢትዮጵያ ለዜጎቿ ምቹ እንድትሆን በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ በመሆኑ የአገሪቱ ቀጣይ ጊዜያት ብሩህ እንደሚሆኑ ተስፋ አለኝ ያሉት አምባሳደሩ፣ በኢትዮጵያ እና በአሜሪካ መካከል ያለው ጥልቅና ታሪካዊ ግንኙነት ወደፊትም ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የእውነተኛ ዴሞክራሲ፣ የማኅበራዊ ፍትሕና የኢኮኖሚያዊ እድሎች አገር እንድትሆንና ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍንባት የአሜሪካ መንግሥት የኢትዮጵያን ሽግግርና ለውጡን ደግፋ መንቀሳቀሷንም አመልክተዋል።
አሜሪካ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላም ያካሄዷቸውን ዘርፉ ብዙ የለውጥ ሥራዎች መደገፏን አስታውቀው፣ ድጋፍ የተደረገው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያነሷቸው ሃሳቦች ከአሜሪካ የዴሞክራሲ መርህ እና እሳቤ ጋር የሚጣጣም በመሆኑ እንደሆነም ገልጸዋል።
“ይህን ተከትሎም አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት አጋርነት እንዲሰፋ ተደርጓል” ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ መንግሥት ያከናወናቸው የለውጥ ሥራዎች ተቋማዊ እንዲሆኑ እና የሚፈለገውን ግብ እንዲመቱ ይበልጥ መሥራት እንደሚገባም ያመለከቱት አምባሳደሩ፣ “ከሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ የነበሩ ዲፕሎማሲያዊ አለመግባባቶች፣ አሜሪካ ድጋፍ መሠረዟ እና የኢትዮጵያ መንግሥት በውስጣዊ ሁኔታ መጠመድ ግንኙነቱ ላይ አሉታዊ ጫና ማሳደሩን አስታውቀዋል።
ተሹሞ የሚመጣው የአሜሪካ አምባሳደር የሀገራቱ ግንኙነት ላይ ይበልጥ መሥራት እንደሚኖርበትም የጠቆሙት አምባሳደሩ፣ ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ሠላም ማስከበርና በቀጣናው ፖለቲካዊ ተሳትፎ ከአሜሪካ ጋር ያላት ግንኙነት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ማስታወቃቸውን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘግቧል።