በችሎታቸው የተመረጡ ተማሪዎች የሚማሩባቸው 50 ትምህርት ቤቶች ሊገነቡ ነው

ጥር 21/2014 (ዋልታ) በሁሉም ክልሎች በችሎታቸው የተመረጡ ተማሪዎች የሚማሩባቸው 50 ትምህርት ቤቶች ሊገነቡ መሆናቸውን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በሁሉም ክልሎች በዓይነታቸው ልዩ የሆኑና የልህቀት ማዕከል የሚሆኑ 50 ትምህርት ቤቶች ይገነባሉ ብለዋል።

ትምህርት ቤቶቹ ቀጣይ የአገር መሪ የሚሆኑ ብቁና ተወዳዳሪ ተማሪዎች የሚፈልቁበት በችሎታቸው ብቻ የሚመረጡ ተማሪዎች የሚማሩባቸው መሆናቸውንም ተናግረዋል።

በትምህርት ቤቶቹ የ8ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት መሠረት ባደረገና የትምህርት ሚኒስቴር በሚያወጣውን መመዘኛ የሚያሟሉ ተማሪዎች የሚማሩባቸው እንደሆኑም ተገልጿል።

በሁሉም ክልሎች በሚገነቡት እነዚህ የልህቀት ማዕከላት ከሁሉም የአገሪቱ ክልሎች የሚመለመሉ ተማሪዎችን ተቀብለው የሚያስተምሩ መሆናቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።