ለኢፍጣር መርኃ ግብር ለተሽከርካሪዎች ዝግ የሚሆኑ መንገዶች ይፋ ሆኑ

ለኢፍጣር ዝግ የሚሆኑ መንገዶች

ሚያዝያ 21/2014 (ዋልታ)

በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ከሚካሄደው ታላቁ የኢፍጣር መርኃ ግብር  ጋር ተያይዞ ለተሽከርካሪ ዝግ የሚሆኑ መንገዶችን የፀጥታና የደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል ይፋ አደረገ፡፡

የከተማዋን ሠላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ ከመላው ሠላም ወዳድ ሕዝብ ጋር ሆኖ ተግባሩን በመወጣት ላይ የሚገኘው የፀጥታና የደኅንነት ግብረ ኃይል የታላቁን ረመዳን ፆምን አስመልክቶ ለሚደረገው የጎዳና ላይ ኢፍጣር መርኃ ግብር  አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አጠናቆ ወደ ሥራ መግባቱን አስታውቋል፡፡

ሠላም ወዳዱ ሕዝብም ለፀጥታ አካላት የሚያደርገውን ቀና ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል የጋራ ግብረ ኃይሉ ጥሪውን አቅርቧል፡፡

በዛሬው ዕለት ከቀኑ 7፡00 ሰዓት ጀምሮ መርኃ ግብሩ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ከቅዱስ ኡራኤል አካባቢ ጀምሮ እስከ መስቀል አደባባይ እና በዙሪያዋ የሚገኙ መንገዶች ለተሽከርካሪዎች ዝግ እንደሚሆኑም ተገልጿል፡፡

በዚህም መሰረት  ከመገናኛ ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ሀያ ሁለት ወይም ዘሪሁን ህንፃ አካባቢ ዝግ ይደረጋል፣ ከወሎ ሰፈር ወደ መስቀል አደባባይ ወሎ ሰፈር ኦሎምፒያ፤ ከጎተራ ወደ መስቀል አደባባይ ለሚመጡ አሽከርካሪዎች አጎና ሲኒማ፤ ከጦር ኃይሎች በሜክሲኮ ወደ መስቀል አደባባይ እና ከሜኪሲኮ ወደ ብሔራዊ ቴአትር ለሚጓዙ ሜክሲኮ አደባባይ፤   ከጌጃ ሰፈርና ከጎማ ቁጠባ በሰንጋ ተራ ወደ መስቀል አደባባይ ለሚጓዙ የቀድሞው ደሳለኝ ሆቴል መስቀለኛ ላይ፤ ከጎማ ቁጠባ ወደ ብሔራዊ ለሚጓዙ ጎማ ቁጠባ ላይ እና ከሜክሲኮ ወደ ፖስታ ቤት ለሚሄዱ ሚትሮሎጂ አካባቢ እንዲሁም ከጥቁር አንበሳ ሼል ወደ ኢሚግሬሽን ለሚሄዱ አሽከርካሪዎች ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በር አካባቢ፤ከተክለኃይማኖት በጎላ ሚካኤል ለሚመጡ ጎላ ሚካኤል መስቀለኛ ላይ እና ከተክለኃይማኖት ወደ ቴዎድሮስ አደባባይ ለሚመጡ ተክለኃይማኖት ቤተ ክርስቲያን እንዲሁም ከተክለ ኃይማኖት በሶማሌ ተራ ወደ ባንኮ ዲሮማ ለሚመጡ አሽከርካሪዎች ሸዋ ሱፐር ማርኬት ጋር ዝግ የሚደረግ ይሆናል፡፡

እንዲሁም ከቀድሞ አትክልት ተራ አካባቢ በአሮጌው ፖስታ ቤት ወደ ቸርችል ጎዳና የሚወስደው መንገድ አሮጌው ፖስታ ቤት፤  ከደጎል አደባባይ ወደ እሪ በከንቱ ደጎል አደባባይ ላይ እና ከአራት ኪሎ በፓርላማ ወደ ውጭ ጉዳይ የሚወስደው መንገድ ሸራተን ሆቴል መውረጃ ላይ፤  ከአራት ኪሎ በብሔራዊ ቤተ መንግስት ወደ መስቀል አደባባይ ለሚጓዙ አሽከርካሪዎች ብሔራዊ ቤተ መንግሥት መስቀለኛ ላይ የሚዘጋ ሲሆን ከካዛንቺስ ሼል ወደ ፍል ውሀና ወደ ባምቢስ የሚወስዱት መንገዶች ካዛንስ ሼል ላይ ከቀኑ 6፡00 ሰዓት ጀምሮ የኢፍጠር ፕሮግራሙ እስከሚጠናቀቅበት ሰዓት ድረስ ዝግ የሚደረጉ ይሆናል፡፡

በተጨማሪም በተገለፁት መንገዶች ላይ ለአጭርም ሆነ ለረጅመ ሰዓታት ተሽከርካሪዎችን አቁሞ መሄድ የተከለከለ ሲሆን ኅብረተሰቡ መርኃ ግብሩ በሠላም ተጀምሮ በሠላም እንዲጠናቀቅና ማንኛውም ዓይነት አጠራጣሪ ነገሮች ሲያጋጥሙ በፖሊስ የመረጃ ስልኮች 0111 11 01 11 እና ነፃ የስልክ መስመር 991 ላይ በመደወልና መረጃ በመስጠት የተለመደ ትብብሩን እንዲያደርግ የፀጥታና የደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታውቋል፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦

ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW