በነጭ ናፍጣ ላይ 80 በመቶ እና በቤንዚን ላይ 75 በመቶ ድጎማ ይደረጋል

መስከረም 28/2017 (አዲስ ዋልታ) በነጭ ናፍጣ ላይ 80 በመቶ እና በቤንዚን ላይ 75 በመቶ ድጎማ እንደሚደረግ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ሚኒስቴሩ መንግሥት ከፍ ያለውን ድጎማ የሚያደርግበት ለአንድ ዓመት የሚዘልቅ የነዳጅ ድጎማ ሥርዓት ተግባራዊ መደረጉንም አመልክቷል፡፡

የነዳጅ ሪፎርም አፈጻጸም የደረሰበትን ደረጃ እና የቀጣይ አቅጣጫ አስመልክቶ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር አማካሪ አህመድ ቱሳ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸውም ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ የተደረገው የነዳጅ የሪፎርም ሥራ ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን በመፍታት ጥሩ የሚባል ውጤት ማምጣቱን አንስተው በዋናነትም መንግሥት ላይ የነበረውን የዕዳ ጫና ያቃለለ፣ ኮንትሮባንድን መቆጣጠር ያስቻለ እና የነዳጅ ግብይትን ፈጣንና ዘመናዊ ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ባለፉት ሦስት ዓመታት ጥቅል ድጎማ ከ197 ቢሊየን ብር በላይ በመንግሥት ድጎማ መደረጉንም ጠቁመዋል።

ለሁሉም የሕዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርቶችም ከጥቅል ድጎማው በተጨማሪ ከ30 ቢሊየን ብር በላይ ድጎማ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

በዚህም የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ በገበያ ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ተጽዕኖ ያገናዘበ የዋጋ ማስተካከያ ስትራቴጂ ተነድፎ ወደ ሥራ እንዲገባ መወሰኑን ተናግረዋል፡፡

የነዳጅ ድጎማ ሥርዓት ተግባራዊ ለማድረግም መንግሥት በዓመት እስከ 300 ቢሊየን ብር ወጪ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ተግባራዊ ከተደረገ ወዲህ መንግሥት ለነዳጅ ከ35 ቢሊየን ብር በላይ ድጎማ ማድረጉንም ገልጸዋል።