በአላማጣ ከተማ ተከማችቶ የነበረ ከ3 ሺሕ ኩንታል በላይ የእርዳታ እህል ተገኘ

ጥቅምት 15/2015 (ዋልታ) በአላማጣ ከተማ አሸባሪው ህወሓት ለታጣቂዎቹ አከማችቶት የነበረው ከ3 ሺሕ ኩንታል በላይ የእርዳታ እህል ተገኝቷል።

አሸባሪውና ወራሪው የወያኔ ቡድን ለራያ አላማጣ ህዝብ የሚመጣውን የእርዳታ እህል ለህዝቡ ሳያደርስ ለታጣቂዎቹ ቀለብ እንዲውል በየ መጋዝኖቹ እና ወፍጮ ቤቶች አከማችቶት መገኘቱን  ነው መረጃው ያመለከተው።

ተከማችቶ የተገኘው የእርዳታ እህልም ከ2 ሺሕ 500 ኩንታል በላይ የUSAID የተፈጨ የስንዴ ዱቄት፣ ከ400 ኩንታል በላይ በUSAID ከረጢት የታሸገ ስንዴ፣ ከ100 ኩንታል በላይ ብስኩቶች እና ኃይል ሰጪ ምግቦች መሆኑም ተገልጿል።

የሽብር ቡድኑ ካለፈው 1 ዓመት ከ4 ወር በላይ በሆነ ጊዜ ውስጥ ለሰብዓዊ እርዳታ እንዲውል የሚገባ የትኛውንም አይነት ድጋፍ ከህዝቡ እየነጠቀ ለታጣቂዎቹ ሲያከማችና ሲቀልብ እንደነበር የአላማጣ ከተማ ነዋሪዎች ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

ወይዘሮ ሰዓዳ አደም የአላማጣ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ፥ ከሐምሌ/2013 ዓ.ም ጀምሮ ምንም ዓይነት እርዳታ ደርሷቸው እንደማያውቅ ገልፀው ልጆቻቸውን ለመመገብ በችግር እና በእንግልት ማሳለፋቸውን በተስፋ መቁረጥ ስሜት ውስጥ ሆነው ተናግረዋል።

አገዳ እየሸጡ እና በቆሎ እየጠበሱ በመሸጥ በሚያገኟት ገቢ ለልጆቻቸው እህል በውድ እንደሚሸምቱ የተናገሩት ወ/ሮ ሰዓዳ አንድ ጣሳ ማሽላ በ250 ብር ይገዙ እንደነበርም ተናግረዋል።

የሽብር ቡድኑ እንኳንስ የእርዳታ እህል ሊሰጠን ቀርቶ ለልጆቻችን ቀለብ በውድ የገዛኋትን ትንሽ ማሽላ አስፈጭቼ ሳላቦካ ዱቄት አምጪ ብለው አስፈራርተው ይወስዱብኛል ብለዋል።

ወይዘሮ ትዕግስት ሙሉ የተባሉ የከተማዋ ነዋሪ በበኩላቸው ለህዝቡ እርዳታ መጥቷል ተብሎ እንሰማለን ነገር ግን እርዳታውን ለህዝቡ አይሰጡም፤ እርዳታውን ለወታደሮቻቸው ስንቅ ሲያደርጉት ነበር ብለዋል።

ለእርዳታ የመጣውን ስንዴ ወፍጮ ቤት ጭነው ወስደው ሌትና ቀን ሲፈጭ ነው የሚውለው፤ የተፈጨውን ዱቄትም ህዝቡ እንዲጋግር እያስገደዱ ያሰራሉ ሲሉ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

በአላማጣ ከተማ በተለያዩ መጋዝኖች እና ወፍጮ ቤቶች ተከዝኖ የተገኘውን የእርዳታ እህል የሰሜን ወሎ ዞን አመራሮች ከፀጥታ ሀይሉ ጋር በመቀናጀት ከተከማቹበት መጋዝኖችን አስቸኳይ ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸውው የራያ አላማጣ ነዋሪ እያከፋፈሉት እንደሚገኙ ተገልጿል።