በአማራ ክልል በዓላት በሰላም እንዲከበሩ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መጠናቀቁን የክልሉ ፖሊስ አስታወቀ

ታኅሣሥ 27/2015 (ዋልታ) በአማራ ክልል የገና በዓልን ጨምሮ በጥር ወር የሚከበሩ ህዝባዊና ሃይማኖታዊ በዓላትን በሰላም ለማክበር አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ስራ መጠናቀቁን የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ።

በኮሚሽኑ የህብረተሰብ አቀፍና የመንገድ ላይ ትራፊክ ደህንነት ምክትል ዘርፍ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ደረጀ አቻምየለህ በዓላቱን በተሳካ መንገድ ለማክበር ተገቢ ዝግጅቶች መደረጋቸውን ገልጸዋል።

መላ ህዝቡ ገና እና ጥምቀትን ጨምሮ ሌሎች ህዝባዊና ሃይማኖታዊ በዓላትን በሰላም እንዲያከበር ማህበረሰቡን ያሳተፈ የንቅናቄ መድረኮችን በመፍጠር ሲሰራ መቆየቱንም አንስተዋል።

ከበዓላት አከባበር ጋር በተያያዘ ሊከሰቱ የሚችሉ ወንጀሎችን ቀድሞ በመለየት በብቃት መከላከል የሚያስችል ስምሪት መሰጠቱንም ጨምረው ገልጸዋል።

ወንጀልን ለመከላከል ፖሊስ ብቻውን አይቻለውም ያሉት ረዳት ኮሚሽነሩ በመሆኑም መላውን ህብረተሰብ በተለይም ወጣቶችን ያሳተፈ የቅድመ ዝግጅት ስራ በስፋት መሰራቱን ተናግረዋል።

ለገና እና ጥምቀት በዓላት በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ዜጎች ወደ ክልሉ የሚመጡ መሆኑን አንስተው እንግዶቹ ያለምንም የፀጥታ ስጋት በዓላቱን ማክበርና የቆይታ ጊዜያቸው እንዲያምር ተሰርቷል ብለዋል።

የሰላም ማስከበር ስራውን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ መላ ህብረተሰቡ ከፀጥታ ኃይሉ ጎን ሆኖ ማገዝ እንዳለበትም ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የፀጥታ ኃይሉ አስቀድሞ ተገቢውን ዝግጅት ያደረገ በመሆኑ ወደ ክልሉ የሚመጣ ማንኛውም ዜጋ በነጻነት በዓላቱን እንዲያከብር መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።