በአማራና አፋር ክልሎች ለሚገኙ 11 ሆስፒታሎች የላቦራቶሪ መሳሪያዎች ድጋፍ ተደረገ

ሐምሌ 27/2014 (ዋልታ) የኦሃዮ ስቴት ግሎባል ዋን ሄልዝ ፕሮግራም በአማራና አፋር ክልሎች በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው 11 ሆስፒታሎች ከ9 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ የላቦራቶሪ መሳሪያዎች ድጋፍ አደረገ።

የጤና ሚንስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ፤ በመጀመሪያው ዙር ድጋፍ ስድስት ሚሊዮን ብር የሚጠጋ የህክምና መሳሪያዎች ድጋፍ መደረጉን አስታውሰዋል።

በሁለተኛ ዙር ደግሞ በአማራና አፋር ክልሎች በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው 11 ሆስፒታሎች ከ9 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ የላቦራቶሪ መሳሪያ ድጋፍ መደረጉን ጠቅሰዋል።

በጦርነቱ ምክንያት ውድመት የደረሰባቸውን የጤና ተቋማት መልሶ ለማቋቋም ሰፊ ርብርብ ቢደረግም እስካሁን በታሰበው ልክ ችግሩን መፍታት አልተቻለም ያሉት ሚኒስትሯ የአጋር አካላት እገዛ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

በኦሃዮ ስቴት ግሎባል ዋን ሄልዝ ፕሮግራም የተደረገው ድጋፍም በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ሆስፒታሎች ወደ ቀደመ ስራቸው ለመመለስ ትልቅ ትርጉም አለው ብለዋል።

የኦሃዮ ስቴት ግሎባል ዋን ሄልዝ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ አባተ፤ ጦርነቱን ተከትሎ በሰሜኑ የአገሪቱ  ክፍል በርካታ ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመት በመድረሱ መልሶ ለማቋቋም ሰፊ ርብርብ እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም በሁለቱም ክልሎች ለሚገኙ አምስት ሆስፒታሎች ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰው ድጋፉ ለሁለተኛ ዙር መደረጉን ገልጸዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

የተደረገው ድጋፍ ክፍተቶችን መሰረት ያደረገ መሆኑን በመግለጽ መሳሪያዎቹ አገልግሎት ሲጀምሩ ለአካባቢው ማህበረሰብ ሰፊ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ነው ብለዋል።

በተመሳሳይ የኮሪያ መንግስትና ኤግዚም ባንክ ለኮቪድ 19 ምርመራ የሚያገለግል የላቦራቶሪ መመርመሪያ ኪት ድጋፍ አበርክቷል።