በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ኤች አር 6600ና ኤስ 3199 የተባሉት አደገኛ ረቂቅ ህጎች እንዳይጸድቁ ሰፊ ዘመቻ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ

ደመቀ መኮንን

መጋቢት 13/2014 (ዋልታ) በመላው አሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የዳያስፖራ ወገኖች በአሜሪካ ምክር ቤቶች በኢትዮጵያ ላይ ለማሳለፍ የታቀዱት እጅግ አደገኛ ረቂቅ ህጎች እንዳይጸድቁ ከፍተኛ ዘመቻ እንዲያደርጉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጥሪ አቀረቡ።

ሚኒስትሩ በመላው አሜሪካ ከሚገኙ የኮሙዩኒቲ አደረጃጀት ኃላፊዎች፣ የታስክ ፎርስ፣ የሲቪክ ማኅበራት አመራሮችና ተወካዮች ጋር ትናንት በዙም ውይይት አድርገዋል።

በአሜሪካ ኮንግረስ እና ሴኔት በኩል በረቂቅ ደረጃ የሚገኙት ኤች አር 6600 እንዲሁም ኤስ 3199 በሚል የቀረቡ ረቂቅ ህጎች ኢትዮጵያዊያን በደም መስዕዋትነት ያስከበሩትን ሉዓላዊነት በእጅ አዙር ለመቀማት የተሸረቡ ሴራዎች ናቸው ብለዋል።

ረቂቅ ህጎቹ ከጸደቁ ኢትዮጵያ ከሌሎች አገራት ጋር የሚኖራት የጸጥታ፣ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ግንኙነት በሌሎች ኃይሎች በጎ ፈቃድ እንዲንጠለጠልና ራሷን የማትከላከል ሽባ አገር የሚያደርግ ነው ብለዋል።

ከዚህም ባሻገር በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኘውን ወገናችን ጨምሮ ዳያስፖራውን ከእናት አገሩ እና ዘመዱ ጋር የሚያቆራርጡ እጅግ አሳሪ እና ታይቶ የማይታወቅ የሉዓላዊነት መቀሚያ ረቂቅ ህጎች ናቸውም ነው ያሉት።

ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል አገሪቱ ገጥሟት የነበረውን ዓለም ዐቀፍ የዲፕሎማሲ ጫና ለመቋቋም ዳያስፖራው ወገናችን ቁር እና ጸሃይ ሳይገታው ላሳየው እውነተኛ አገር ወዳድነት ምስጋና ያቀረቡት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አነዚህ ረቂቅ ህጎችም እንዳይጸድቁ ከምንጊዜውም በላይ በተቀናጀ የአንድነት ዘመቻ እንዲንቀሳቀሱ ጠይቀዋል።

መንግሥት እየወሰዳቸው የሚገኙ እርምጃዎች አገርን ያስቀደሙ እና ዘላቂ ሰላምና አንድነትን ታሳቢ በማድረግ የሚወሰኑ መሆናቸውን ጠቁመው በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ መቼም ቢሆን እንደማይደራደር ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ያለትን ረጅም ዘመን ያስቆጠረ ግንኙነት እንዲጠናከር ሁሌም ዝግጁ መሆኗን የገለጹት ሚኒስትሩ ሉዓላዊነቷን የሚጋፉ የእጅ አዙር ጥምዘዛዎችን ግን እንደማትቀበል ነው ያረጋገጡት።

አምባሳደር ፍጹም አረጋ

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ በበኩላቸው ዳያስፖራው በየአካባቢው ያሉ የመንግሥት ተመራጮችን በስልክ፣ በኢሜል፣ ፊርማ በማሰባሰብና በአካል እያገኘ የረቂቅ ህጎቹን አፍራሽነት እንዲያስረዳ ጥሪ አቅርበዋል።

በውይይቱ ላይ የተገኙ ተሳታፊዎችም ረቂቅ ህጎቹ የመንግሥትና የፓርቲ ሳይሆኑ የአገርን አንድነትና ቀጣይነት አደጋ ላይ የሚጥሉ በመሆናቸው ከምንጊዜውም በላይ በቅንጅት በመስራት ባሉበት እንዲመክኑ እንደሚሰሩ ቃል መግባታቸውን በአሜሪካ ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።