በአምቦ አሸባሪዎቹን ሕወሓትንና ሸኔን የሚያወግዝና መከላከያን የሚደግፍ ሰልፍ እየተካሄደ ነው

ጥቅምት 28/2014 (ዋልታ) የምእራብ ሸዋ ህዝብ አሸባሪዎቹን ሕወሓትና ሸኔን በማውገዝና ጀግናው መከላከያ ሰራዊትን በመደገፍ በአምቦ ህዝባዊ ሰልፍ እያካሄደ ነው፡፡
በሰልፉ አምቦ ከተማን ጨምሮ በዞኑ ከሚገኙ ወረዳዎች የተወጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች በመሳተፍ ላይ ናቸው።
ሰልፈኞቹ የሸብርተኞቹን የሕወሓትና ሸኔን ኢትዮጵያን የማፍረስ ዓላማና ህልም ለማምከን ዝግጁ መሆናቸውን እየገለጹ ናቸው፡፡
የአሸባሪዎቹን ሀገር የማጥፋት የጭካኔ ድርጊቶችን አንድ ሆነን እንመክታለን፤ ኢትዮጵያ ለጠላት ተንበርክካ አታውቅም፣ ሸኔና ወያኔ የኦሮሞ ጠላቶች ናቸው፣ የኦሮሞ ህዝብ ለወያኔ እጁን አይሰጥም፣ ወያኔና ሸኔ የቀሬና ቄሮ ዋና ጠላቶች ናቸው የሚሉ መፈክሮችን በማስተጋባት ህወሀትና ሸኔን እያወገዙ ይገኛሉ።
ክብር ለመከላከያ ሰራዊታችን፣ መከላከያ ሰራዊት ሃይላችን ነው፣ መከላከያ ሰራዊት አጥራችን ነው፣ ይጠብቀናል እናከብረዋለን፣ አከባቢዬን እጠብቃለሁ ሀገሬን ለማዳን እዘምታለው የሚሉና መሰል መፈክሮችንም በማስተጋባት ለመከላከያ ሰራዊት ድጋፋቸውን በማሰማት ላይ ናቸው።
“የሕወሓት ተልዕኮን የሚያስፈፅሙ በየአካባቢው ተሰግስገው የሚገኙ ባንዳዎችን በማጋለጥ የበኩላችንን እንወጣለን” ሲሉም በጋራ ቃል እየገቡ ናቸው።
ኢዜአ እንደዘገበው በጀግኖቻችን ደምና አጥንት የተገነባች ኢትዮጵያ ሀገራችን በአሸባሪዎቹ የህወሓትና ሸኔ ድርጊት አትፈርስም” ሲሉም ድምጻቸውን እያሰሙ ይገኛሉ።