አዲስ አበባ፣ የካቲት 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም የኢኮኖሚ ስርዓትን በመገንባት ሂደት የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ጠየቁ።
በአየር ንብረት ለውጥ አጀንዳ የግሉን ዘርፍ ፋይናንስ ነክ ተሳትፎን ለማጠናከር ያለመ ዐውደ-ጥናት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
በዐውደ-ጥናቱ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ÷ ኢትዮጵያ የፓሪስ ስምምነትን ጨምሮ ዓለም አቀፍ አየር ንብረት ለውጥ ስምምነቶችን ተቀበላ እየተገበረች ነው ብለዋል።
በመሪ የልማት ዕቅዷ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ትልቅ ትኩረት እንደተሰጠው በመጠቆም።
የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም የኢኮኖሚ ስርዓትን በመገንባት ሂደት የግሉ ዘርፍ በንቃትና በመሪነት እንዲሳተፍም ጠይቀዋል።
ለአብነትም በአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም በሚያስፈልጉ የፋይናንስ አቅርቦት ረገድ የግሉ ዘርፍና የመንግሥት አጋርነትን ማጠናከር እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
የዓለም አቀፉ የአረንጓዴ ልማት ኢንስቲትዩት የኢትዮጵያ ተወካይ ዳንኤል ኦቦናያ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ መቋቋም ውጤታማ ተግባራት እያከናወነች መሆኗን አድንቀዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።