ሚያዝያ 07/2013 (ዋልታ) – በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር በአራዳ ክፍለ ከተማ በተያዘው በጀት ዓመት ከ130 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተገነቡ 48 ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት ዝግጁ መሆናቸው ተገለጸ፡፡
ፕሮጀክቶቹን በአራዳ ክፍለ ከተማ ብልጽግና ፓርቲን ወክለው የሚወዳደሩ እጩዎች፣ የክፍለ ከተማው አመራሮች እንዲሁም የፓርቲው አባላት ጎብኝተዋል፡፡
የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ኢንጂነር ያየ አማረ እንደገለጹት፣ ክፍለ ከተማው ፕሮጀክቶችን መጀመር ብቻ ሳይሆን ለማጠናቀቅ እየሰራ ነው፡፡
በዚህም በተያዘው በጀት ዓመት ከተጀመሩት 51 ፕሮጀክቶች እስካሁን 48ቱ ለአገልግሎት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ቀሪዎቹ ፕሮጀክቶች እስከ በጀት ዓመቱ መገባደጃ ድረስ ይጠናቀቃሉም ብለዋል፡፡
ለአገልግሎት ዝግጁ ከሆኑ ፕሮጅክቶች መካከል በትምህርት ቤቶች የተገነቡ 22 የተማሪዎች መመገቢያ አዳራሾች እንዲሁም የማብሰያ ቦታዎች እንደሚገኙባቸው ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም ሰባት የስፖርት ማዘውተሪያ ሜዳዎች፣ የጤና ጣቢያ እድሳት፣ የወረዳ አስተዳደር ህንጻዎች እድሳትና በሶስት ትምህርት ቤቶች የተገነቡ ሶስት ዘመናዊ የመጸዳጃ ቤቶች ይገኙባቸዋል፡፡
የአራዳ ክፍለ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሚደቅሣ ከበደ በበኩላቸው፣ በፕሮጀክቶች መካከል በትምህርት ቤቶች ላይ የተገነቡት ግንባታዎች ፓርቲው ለመጪው ትውልድ ራዕይና ግብ መሳካት የሚሰራ መሆኑን ያሳያል ብለዋል፡፡
እንደ ኢዜአ ዘገባ ፕሮጀክቶችን በፍጥነትና በጥራት ማጠናቀቅ እንደ ባህል ተደርጎ መወሰድ አለበትም ነው ያሉት።