በአርሲ ዞን 20 የአሸባሪው ሸኔ አባላት እጃቸውን ሰጡ


ኅዳር 11/2014 (ዋልታ)
በአርሲ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች 20 የአሸባሪው ሸኔ አባላት ለመንግሥትና አባገዳዎች በሰላም እጅ መስጠታቸው ተገለፀ።
የዞኑ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ ኮሚቴ ሰብሳቢና የዞኑ ዋና አስተዳደሪ ሙሳ ፎሮ በወረዳው አገር ለማፍረስ ከተሰለፉ ጠላቶች ጋር መሰለፍን ያልፈቀዱ 20 የሸኔ አባላት እጃቸውን በሰላም ሰጥተዋል ብለዋል።
በሙኔሳ ወረዳ በተካሄደው ሰላም ጉባኤ ላይ አባገዳዎች በአሸባሪው ሸኔ ላይ የውግዘት ውሳኔ አሳልፈዋል።
በተሳሳተ አመለካከት የሽብር ቡድኑን ተቀላቅለው ሲንቀሳቀሱ ቆይተው የአባገዳዎችን የውግዘት ውሳኔና ጥሪ ተቀብለው እጅ ሊሰጡ እንደቻሉ ገልጸዋል።
የአርሲ አባገዳዎች ‘ልጆቻችን ከባንዳ ጋር አይወግኑም፣ ሀገር አያፈርሱም፣ መክረን ገስፀን እንመልሳለን’ ብለው ቃል በገቡት መሰረት አባላቱ ከጥፋት መንገድ በመለለስ እጃቸውን በሰላም መስጠታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በሀሰት ፕሮፓጋንዳ ተታለው ጫካ ገብተው የነበሩት እነዚህ የአሸባሪው ሸኔ ቡድን አባላት ሰላማዊ መንገድ መምረጣቸውን ተናግረዋል።
አባገዳዎችና ማኅበረሰቡ ባደረጉት የተቀናጀ ዘመቻ ቀደም ሲልም በርካታ የአሸባሪው ሸኔ አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም አስታውቀዋል።