በአርቲስት ተስፋዬ ገሰሰ ስም ፋውንዴሽን ተቋቋመ

ጥር 13/2014 (ዋልታ) በአንጋፋው አርቲስት ተስፋዬ ገሰሰ ስም ነፃ የትምህርት ዕድል ማመቻቸትን ጨምሮ በኪነ ጥበቡ ዘርፍ የሚሰራ ፋውንዴሽን መቋቋሙ ተገለፀ።

አርቲስት ተስፋዬ በርካታ የኪነ ጥበብ ሥራዎችን ለኢትዮጵያ ያበረከቱ ሲሆን በኢትዮጵያ የቴአትር ተቋማት ውስጥ አበርክቷቸው የላቀ የሆኑ ወጣት የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችን አፍርተዋል።

በስማቸው አዲስ የተቋቋመው ፋውንዴሽን የቦርድ ሊቀ መንበር ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ “በኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ ውስጥ ታላቅ አሻራ ላኖረው የኪነ ጥበብ ሰው ስሙ እና ሥራው እንዳይዘነጋ ቋሚ የሆነ ፋውንዴሽን ማቋቋም ተገቢ ነው” ብሏል።

ፋውንዴሽን በኪነ ጥበቡ ዘርፍ ነፃ የትምህርት እድል ይሰጣል፣ ጥናት እና ምርምሮችን ያካሂዳል ፣የተለያዩ የኪነ ጥበብ ሥራዎች እንዲዘጋጁ መድረኮችን ያመቻቻል ተብሏል።

እሁድ በላፍቶ ሞል በሚከናወን ዝግጅት ፋውንዴሽኑ ሥራ ይጀምራል ተብሏል።

በቁምነገር አህመድ