በአሸባሪው ሕወሓት የወደሙ ተቋማትን መልሶ ለመገንባት የቻይና መንግሥት ድጋፍ ተጠየቀ

መጋቢት 7/2014 (ዋልታ) በአማራ ክልል በአሸባሪው የሕወሓት ቡድን የወደሙ መሰረተ ልማቶችና ተቋማትን መልሶ ለመገንባት እየተደረገ ባለው ጥረት የቻይና መንግሥት የልማት ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) ጠየቁ።
በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዣኦ ዢዩአን የተመራ ልኡክ ከአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) ጋር በባሕር ዳር ከተማ ውይይት እያደረገ ነው።
በውይይቱ ላይ ርዕሰ መስተዳድር እንደገለፁት አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በአማራ ክልል በወረራ በቆየባቸው ጊዜያት በርካታ መሰረተ ልማቶችን አውድሟል ዘርፏል።
አሁን ላይ የወደሙና የተዘረፉ መሰረተ ልማቶችና ተቋማትን መልሶ ለመገንባት ሰፊ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።
የቻይና መንግሥትም የቀደመውን ወዳጅነትና የልማት አጋርነት አጠናክሮ ከማስቀጠል አንፃር በመልሶ ግንባታ ሥራ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ርዕሰ መስተዳደሩ ጠይቀዋል።
የቻይና መንግሥት የወደሙ ተቋማትን መልሶ ለመገንባት እየተደረገ ባለው ጥረት እንዲሁም እንደ አገርም ሆነ እንደ ክልል በኢንዱስትሪ፣ በግንባታ፣ በግብርናና ሌሎች ዘርፎች እያደረገ ያለውን የልማት ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
“የቻይና መንግሥትና ሕዝብ እንደ አማራ ክልልም ሆነ እንደ ኢትዮጵያ ያለው ግንኙነት በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ እና በዲፕሎማሲ ብቻ ሳይሆን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ ጠንካራ ነው “ብለዋል።
ውይይቱ በክልሉ ወቅታዊ ሁኔታና ዘላቂ ልማት ላይ ያተኮረ ሲሆን በተለያዩ ስፍራዎች ጉብኝት ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።