በአሸባሪው ሕወሓት ፈርሶ የነበረው የአልውሃ ድልድይ ጥገና ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ

የአልውሃ ድልድይ

ታኅሣሥ 27/2014 (ዋልታ) በአሸባሪው የሕወሓት ቡድን ፈርሶ የነበረው የአልውሃ ድልድይ ጥገና ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ።

ቡድኑ የደረሰበትን ምት መቋቋም ሲያቅተው እና ሲፈረጥጥ የአልውሃን ድልድይ አፍርሶ መሄዱ ይታወቃል።

አካባቢው ከአሸባሪው ቡድን ነጻ መሆኑን ተከትሎ የተጀመረው የአልውሃ ድልድይ የጥገና ስራ በዛሬው ዕለት ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል፡፡

የአልውሃ ድልድይ ፕሮጀክት መሃንዲስ ኢንጅነር ዮሐንስ አያሌው እንደገለጹት የድልድዩ የጥገና ስራ በሰባት ቀናት ውስጥ ተጠናቋል።

የድልድዩ ግንባታ ሙሉ በሙሉ በብረት የተከናወነ መሆኑን ገልጸው 55 ሜትር ገደማ ርዝመት እንዳለውም ተናግረዋል።

ድልድዩም 60 ቶን ወይም 600 ኩንታል የመሸከም አቅም እንዳለው ጠቅሰው ከሚሰጠው አገልግሎት አኳያ ከፍተኛ ወጪ ተደርጎበት በአጭር ጊዜ ውስጥ የጥገና ስራው እንዲከናወን መደረጉን አመልክተዋል።

የድልድዩ ግንባታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊጠናቀቅ የቻለውም የኮምቦልቻ ዲስትሪክት የወልዲያ ሴክሽን ሰራተኞች ሌት ተቀን በቁጭት ባከናወኑት ስራ መሆኑንም አመልክተዋል።

ድልድዩ ረጅም ጊዜ አገልግሎት መስጠት እንዲችል ጥራቱን ጠብቆ መጠገኑንም ነው የገለጹት፡፡

የአካባቢው ኅብረተሰብና አሽከርካሪዎች በድልድዩ መልሶ መገንባትና ለአገልግሎት መብቃት በመቻሉ የተሰማቸውን ደስታ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።