በአሸባሪው የወደሙ ተቋማት ከነበራቸው ቁመና በተሻለ ይደራጃሉ – ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው

ታኅሣሥ 15/2014 (ዋልታ) በአሸባሪው ሕወሓት ወራሪ ቡድን የወደሙ ተቋማት ከነበራቸው ቁመና በተሻለ ይደራጃሉ ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደኅንነት አማካሪ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ተናገሩ፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር የደኅንነት አማካሪ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው በደሴ ከተማ በአሸባሪው ሕወሓት የወደሙ ተቋማትን ጎብኝተዋል።

ሚኒስትሩ የደሴ ቲሹ ካልቸር ማዕከል፣ የደሴ አጠቃላይ ሪፈራል ሆስፒታል፣ የወሎ ዩኒቨርስቲና በከተማዋ የወደሙ ሆቴሎችን ነው የጎበኙት።

ትናት በወልዲያ ከተማ ዛሬ ደግሞ በደሴ ከተማ የወደሙ ተቋማትን ተመልክቻለሁ ያሉት ሚኒስትሩ አሸባሪው የትሕነግ ወራሪ ኃይል ለወረራ በገባባቸው ቦታዎች ሁሉ ያደረሰው ጥፋት ኢትዮጵያ እስካሁን ከገጠማት የውጭ ወረራ የበለጠ ጉዳት ያደረሰና በታሪክም እስካሁን ያልተነበበ ውድመት አድርሷል ብለዋል።

የሕዝብ መገልገያ የሆኑ የትምህርት ተቋማት፣ ሆስፒታሎችና ሆቴሎች በማውደም ማኅበረሰቡን ለመጉዳት በማሰብ ጉዳት ማድረሳቸው የዘቀጠ አስሳሰብ ላይ መውደቃቸውን ያሳየ ነው ሲሉም የጠቅላይ ሚኒስትር የደኅንነት አማካሪው ተናግረዋል።

በምንይሉህ ደስይበለው