በአሸባሪዎቹ ትሕነግ እና ሸኔ ለተጎዱ አካባቢዎች ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ ተገለፀ

ታኅሣሥ 14/2014 (ዋልታ) በአሸባሪዎቹ ትሕነግ እና ሸኔ ለተጎዱ አካባቢዎች ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስታወቀ፡፡
ቋሚ ኮሚቴው የግብርና ሚኒስቴር፣ የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር እና የውሃና ኢነርጅ ሚኒስቴርን የአስር እና አምስት ዓመት እቅዶች ገምግሟል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ሰለሞን ላሌ እንደገለጹት አሸባሪ ቡድኖቹ በአማራ፣ አፋር እና ኦሮሚያ ክልሎች ያደረሱትን ጉዳት ታሳቢ ያደረገ እቅድ ተነድፎ መሰራት አለበት፡፡
በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸው አካባቢዎች የኤሌክትሪክ ኃይል፣ ንፁህ የመጠጥ ውሃ እና የግብርና ግብዓት አቅርቦቶች ስርጭት እንዲኖር ሦስቱም ሚኒስቴሮች የጋራ እቅድ በማውጣት ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸውም ሰብሳቢው ሰለሞን አሳስበዋል፡፡
አክለውም መስሪያ ቤቶቹ የአገሪቱ ከፍተኛ ሃብት የሚፈስባቸው ተቋማት እንደመሆናቸው ብልሹ አሰራሮችን በመታገል ፍትሓዊ እና ተደራሽነት ያለው አገልግሎት እንዲሰጡ በቁርጠኝነት መስራት ይገባል ማለታቸውንም የምክር ቤቱ መረጃ አመልክቷል፡፡