በአቃቂ ቃሊቲ ያለአግባብ በመጋዘን ውስጥ ተከማችቶ የተገኘ ከ19 ሺሕ ሊትር በላይ የምግብ ዘይት ተያዘ

መጋቢት 2/2014 (ዋልታ) በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 በወቅቱ ለኅብረተሰብ መሰራጨት የነበረበት እና ያለአግባብ በመጋዘን ውስጥ ተከማችቶ የተገኘ ከ19 ሺሕ ሊትር በላይ የምግብ ዘይት መያዙ ተገለጸ።

የምግብ ዘይቱ የተያዘው በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 አስተዳደር በተለምዶ አባኮት ተብሎ በሚጠራ አካባቢ በርበሮ የተሰኘ ድርጅት ውስጥ መሆኑ ተገልጿል።

ሰው ሠራሽ የኑሮ ውድነት እና የዋጋ ንረት የሚፈጥሩ ነጋዴዎች እና ግለሰቦችን ለመቆጣጠር የተቋቋመው ግብረ ኃይል ከሌሎች የሕግ አስከባሪዎች ጋር በመሆን በተደረገው ክትትል መያዝ እንደተቻለ ተመላክቷል።

የተያዘው ዘይት በወረዳ 7 ነዋሪዎች ሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበር በኩል ለኅብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እንደሚከፋፈልም ግብረ ኃይሉ ማሳወቁን ከከንቲባ ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።