በአየር ንብረት ጉባዔው አፍሪካ በቂና ተገማች የገንዘብ ካሳ ለማግኘት እንደምትሞግት ተገለጸ

ጥቅምት 27 ቀን 2015 (ዋልታ) “አፍሪካ ለመልከ ብዙ ቀውስ የዳረጋትን የአየር ንብረት ለውጥ ለመቋቋም ዓለም በቂና ተገማች ፋይናንስ የሚያቀርብበት ስርዓት እንዲፈጠር መሞገት የ27ኛው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ጉባዔ አንደኛው አጀንዳዋ ነው” ሲል የአፍሪካ የምግብ ሉዓላዊነት ጥምረት ገለጸ።

27ኛው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ጉባዔ ዛሬ በግብጽ ሻርም አል ሼክ ከተማ መካሄድ የጀመረ ሲሆን፤ በርካቶች ጉባኤውን ‘የአፍሪካ ጉባዔ’ በማለት እየገለጹት ነው።

ተቀማጭነቱን በኡጋንዳ ካምፓላ ያደረገው የአፍሪካ የምግብ ሉዓላዊነት ጥምረት (አሊያንስ ፎር ፉድ ሶቨርኒቲ ኢን አፍሪካ) የተሰኘው ድርጅትም በጉባኤው የአፍሪካ አጀንዳዎች በጉልህ መስተጋባት እንዳለባቸው ያምናል።

የጥምረቱ አስተባባሪ ሚሊዮን በላይ (ፒኤችዲ) እንዳሉት፤ በጉባዔው የአየር ንብረት በካይ ጋዞችን ልቀት መቀነስ፣ ተጽዕኖ መቋቋም እና ፋይናንስ አጀንዳዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ያነሳሉ።

በተለይም እንደ አፍሪካ የግብርና ብዝሃነትንና ከተፈጥሮ ጋር የተስማማ ግብርናን ወይም አግሮ ኢኮሎጂ ዕውን ማድረግ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጠው ገልጸዋል።

የአፍሪካ ጉዳይ የፖለቲካ መልክ እንዳለው ጠቅሰው፤ ለአብነትም በኮቪድ 19 ወረርሽኝ እንዲሁም በሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ሳቢያ አፍሪካ በኢኮኖሚው መስክ ከፍተኛ ፈተና እንደደረሰባት አመልክተዋል።

በዚህም ለአፍሪካ የምግብ ሉዓላዊነት የሕልውና ጉዳይ በመሆኑ፤ ከተፈጥሮ ጋር የተጣጣመ የእርሻ ብዝሃነትና ምርታነማነትን ማሳደግ በጉባኤው ከሚነሱ የአፍሪካ ዐቢይ ትኩረቶች መካከል እንደሚጠቀሱ ነው የገለጹት።

በዚህም ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ብዙ አበርክቶ የሌላት፤ ይልቁንም የከፋ የአየር ንብረት ለውጥ ቀውስ ገፈት ቀማሽ የሆነችው አፍሪካ፤ በቂና ተገማች የሆነ የገንዘብ ካሳ ክፍያ እንደሚያስፈልጋት ተናግረዋል።

በጉባኤው አፍሪካን ለሁለንተናዊ ቀውስ የዳረጋት የአየር ንብረት ለውጥ በተመለከተ ዓለም እንዴት መካስ አለባት? የሚለው ጉዳይ በዋነኛነት ይስተጋባል ማለታውን የኢዜአ ዘገባ አመላክቷል።

ዛሬ በግብጽ ሻርም አል ሼክ ከተማ የተጀመረው 27ኛው የአየር ንብረት ጉባኤ እስከ ሕዳር 9 ቀን 2015 ዓ.ም የሚቆይ ሲሆን ከ190 አገራት በላይ የተወጣጡ ተወካዮች ይሳተፉበታል።