በአዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ የተከለሱ የቅድመ ምረቃ ስርዓተ-ትምህርት ፕሮግራሞች ተግባራዊ እየተደረጉ ነው – ሚኒስቴሩ

የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር

ሚያዝያ 06/2013 (ዋልታ) – አዲሱን የትምህርት ፍኖተ ካርታ መሰረት በማድረግ የተከለሱ የቅድመ ምረቃ ስርዓተ-ትምህርት ፕሮግራሞች ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሚኒስቴሩ የከፍተኛ ትምህርት አካዳሚክ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል ዶክተር ኤባ ሚጄና እንደገለጹት፤ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ጥናት ምክረ ሃሳቦችን መሰረት በማድረግ የከፍተኛ ትምህርት ፕሮግራሞች እና የተግባቦት ክህሎትን የሚያሳድጉ ኮርሶች የተካተቱባቸው የአንደኛ አመት የጋራ ኮርሶች ለሁሉም አዲስ ገቢ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እየተሰጡ ይገኛሉ፡፡

ሁሉም የቅድመ ምረቃ ፕሮግራሞች የሀገሪቱን አዳዲስ የልማት ፍላጎቶች የሚያሳኩ፣ በእውቀት፣ ክህሎት እና አመለካከት የበቁና የዳበሩ ምሩቃንን ከማፍራት ጎን ለጎን በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማስቻል የስርአተ ትምህርት ክለሳና ግምገማ ወሳኝ ሚና እንዳለውም ገልጸዋል፡፡

በመተግበር ላይ ያሉት ፕሮግራሞች በተማሪዎች እውቀት፣ ክህሎት እና አመለካከት ግንባታ ላይ ለውጥ ማምጣት እንደሚችሉ እምነት ተጥሎባቸዋልም ነው ያሉት፡፡

በአዲስ አበባ፣ በሃረማያ፣ ዲላ፣ ደብረማርቆስ፣ ጂማ፣ ባህርዳር እና ጎንደር ዩኒቨርሲቲዎች አስተናጋጅነት የዩኒቨርሲቲ ተወካዮች፣ የኢንዱስትሪ ባለቤቶችና አመራሮች፣ የሙያ ማህበራት ተወካዮች እንዲሁም የተገልጋዩ ማህበረሰብ ወኪሎች በተገኙበት በተከለሰው የስርዓተ ትምህርት ፕሮግራሞች ላይ ውይይት እየተደረገ እንደሚገኝ ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።