በአዲስ አበባ በቅርስነት ለተመዘገቡ 138 ቤቶች የቅርስ ምዝገባ የምስክር ወረቀት ተሰጠ

የካቲት 8/2014 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ባህል ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ በከተማዋ በታሪካዊ ቅርስነት ለተመዘገቡ ለ138 ቤቶች የቅርስ ምዝገባ የምስክር ወረቀት ሰጠ።

የቢሮው ኃላፊ ሂሩት ካሳው (ዶ/ር) በአዲስ አበባ የሚገኙ ቅርሶችን ለመለየት ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ምዝገባ መካሄዱን ገልጸዋል።

የእውቅና ምስክር ወረቀቱ የቅርስ ባለይዞታዎች ቅርሱን ተንከባክበው ለቀጣይ ትውልድ እንዲያስተላልፉ ኃላፊነት የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል።

በቢሮው የቅርስ ጥገና እና እንክብካቤ ዳይሬክተር ደረጀ ስዩም በ2013 በተካሄደው የቅርስ መመዝገብና የመከለስ ሥራ 316 ቅርሶች መለየታቸውን አስታውሰዋል።

ከተለዩት ቅርሶች መካከል ለ138ቱ የእውቅና ሰርተፍኬት መሰጠቱን ገልጸው በቀጣይ ደግሞ ለቀሪዎቹ የምስክር ወረቀት ይሰጣል ብለዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።