በአዲስ አበባ በከፍተኛ ደረጃ ለጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ 135 ስፍራዎች አሉ


ሰኔ 20/2016 (አዲስ ዋልታ) በአዲስ አበባ 135 ከፍተኛ የጎርፍ ተጋላጭነት የሚታይባቸውና አስቸኳይ ምላሽ የሚያስፈልጋቸው ቦታዎች መኖራቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።

በኮሚሽኑ የአደጋ ስጋት ጥናትና ትግበራ ዳይሬክተር ሂሩት ሽፈራው ለአዲስ ዋልታ ዲጂታል ሚዲያ እንደገለጹት ለጎርፍ አደጋ ስጋት የሆኑ ቦታዎች ተለይተዋል።

በዚህም በከተማ አስተዳደሩ 218 ለጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ ቦታዎች መለየት መቻሉንና ከዚህም ውስጥ 135ቱ ከፍተኛ የጎርፍ ተጋላጭነት የሚታይባቸውና አስቸኳይ ምላሽ የሚያስፈልጋቸው ናቸው ብለዋል።

እነዚህን ቦታዎች ለሚመለከታቸው ባለድርሻ ተቋማት የማሳወቅ ስራ የተሰራ ቢሆንም እስካሁን በጉለሌ፣ ቦሌ፣ ኮልፌ፣ አቃቂ ቃሊቲና ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተሞች የሚገኙ 10 ቦታዎች ሙሉ በሙሉ ምላሽ እንዳገኙ እና ቀሪዎቹ በሂደት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ቦታዎቹን ለሚመለከታቸው ባለድርሻ ተቋማት ያሳወቁ ቢሆንም ሙሉ በሙሉ ግን ምላሽ አላገኙም። ለዚህም የተቋማት ቅንጅታዊ አሰራር ክፍተት መኖር፣ ከከተማ ልማት ስራዎች ጋር ተያይዞ ትኩረት ያለማግኘት፣ የበጀት እጥረት መኖር እና ከወሰን ማስከበር ጋር ተያይዞ ያሉ ጉዳዮች እንደ ችግር ማጋጠሙን አንስተዋል።

እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ ቦታዎች በየክፍለ ከተማው እንደሚገኙና አዲስ ከተማ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ ቦሌ፣ ልደታ እና ለሚኩራ ክፍለ ከተሞች ለአብነት ተጠቅሰዋል።

በየአካባቢው በቆሻሻ የተዳፈኑ ቦታዎችን በባለሙያዎች ክትትል በማድረግ ከየአካባቢው ኅብረተሰብ ጋር የማጽዳት ስራ በንቅናቄ እየተሰራ መሆኑንና ኅብረተሰቡ ቆሻሻውን በአግባቡ መጣል ባለበት ቦታ እንዲጥል የማስገንዘብ ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ማፋሰሻ መስመሮች አለመኖር ሌላው ለጎርፍ አደጋ ምክንያት በመሆኑ በሌለበት እንዲሰራ እና የተበላሹ እንዲጠገኑ የማድረግ ስራዎችም ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር እየተሰራ ነው ብለዋል።

በተለያዩ ቦታዎች የተቆፈሩ ጉድጓዶች ውኃ በማቆር በልጆችም ሆነ በኅብረተሰቡ ላይ ጉዳት እንዳያደርስ የመድፈንና ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸው ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ ቦታዎች መፍትሔ ለመስጠት የሚመለከታቸው አካላት ተባባሪ እንዲሆኑም ጥሪ አቅርበዋል።

በአድማሱ አራጋው