በአገሪቱ ጠንካራ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን አስጠብቆ ለማቆየት ሁሉም የድርሻውን እንዲያበረክት ተጠየቀ

አምባሳደር ጀማል በከር

ጥር 6/2014 (ዋልታ) በባህሬን የኢፌዴሪ ቆንስል ጄነራል አምባሳደር ጀማል በከር በባህሬን ከኢትዮጵያ የኮሙዩኒቲ አመራሮች ጋር በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ወይይት አካሂደዋል፡፡

በውይይቱ አገሪቱ የገጠማትን ፈተና ለማለፍና በዘላቂነት ጠንካራ ኅብረ ብሔራዊና ሉዓላዊ አንድነቷን አስጠብቆ ለማቆየት ሁሉም አካላት የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ አምባሳደር ጀማል ጠይቀዋል፡፡

አሁን ከገጠሙን ዘርፈ ብዙና ውስብስብ ችግሮች ፈጥነን በመውጣት ኅልውናውን በዘላቂነት ለማረጋጋጥ ለሠላም ግንባታ ትኩረት በመስጠት ሰላማዊ ውይይቶችን መደገፍ እንደሚያስፈልግም ተገልጿል።

ለዚህም በቅርቡ የተቋቋመው የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን በገለልተኝነት ይህን ትልቅ ተልዕኮ መፈፀም የሚችል ተቋምና አመራር እየገነባ የሚገኝ መሆኑንም አንስተዋል።

በባህሬን የኢትዮጵያ የኮሙዩኒቲ አመራር አባላት በበኩላቸው መንግስት እያደረገ ያለውን የሰላምና የዴሞክራሲ ግንባታ ለአገሪቱ ዘላቂ ሰላምና ብሔራዊ ጥቅም የሚያስከብር መሆኑን በመገንዘብ ከስሜት ነፃ በመሆን ከፊታችን የተጋረጠውን ፈተና በሰከነ ሁኔታና በአስተዋይነት ማለፍ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና አንድነቷን ጠብቃ እንድትቀጥል የተጀመሩትን የሰላምና የዴሞክራሲ እንዲሁም የመልሶ ግንባታ እንቅስቃሴዎች ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ዳያስፖራው የማይተካ ሚና በመጫወት የበኩሉን ድርሻ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት መገለጹን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃልአቀባይ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡