በአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም መሠረት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የግማሽ ዓመት ሥራ አፈጻጸም ተገመገመ

የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሐግብር ዋና አካል የሆነው የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ውጤታማነት ለማሻሻል፣ ተወዳዳሪነታቸውን ለማጎልበት እና የአገልግሎት አሰጣጣቸውን ቀልጣፋ እንዲሆኑ ለመደገፍ ያተኮረ ለአምስት ቀናት የሚቆይ ውይይት ተጀምሯል።

በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታ እና አስተዳደር ኤጀንሲ ስር በሰባት ዘርፎች ማለትም በትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ፣ በግብርና እና አግሮ ኢንዱስትሪ፣ በአምራች ኢንዱስትሪ እና ምሕንድስና፣ የንግድ እና የአገልግሎት ዘርፍ፣ የፋይናንስ ተቋማት፣ የኮሙዩኒኬሽን እና የኮንስትራክሽን ስር ተመድበው የሚገኙ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በ2013 በጀት ዓመት በመጀመሪያው አጋማሽ የነበራቸውን የሥራ አፈጻጸም ግምገማ እየተካሄደ ይገኛል።

ግምገማው ለሁሉም የልማት ድርጅቶች የኦዲት ሪፖርት ላይ የተሰጡ የማሻሻያ ሐሳቦችን ተግባራዊነት እንዲያረጋግጡ ትኩረት መስጠቱ ተገልጿል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ መንግሥት የልማት ድርጅቶቹን ለመደገፍ የቴክኒክ ኮሚቴዎችን አዋቅሮ ሲሠራ መቆየቱን አስታውሰው፣ በተለይም ሁሉም የልማት ድርጅቶች ዓለም አቀፍ የፋይናንስ አስተዳደር እና ሒሳብ አያያዝ ሥርዓት ተከትለው እንዲተገብሩ በመደረጉ የአሠራር መሻሻሎች እየተገኙ ነው ብለዋል።

ሚኒስትሩ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን የዕዳ መጠን ዘርዝሮ በማጥናት እና የመክፈል አቅማቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን የዕዳ ጫና በማቃለል እና ውጤታማ ሆነው እንዲዘልቁ ለማስቻል የሚያግዝ የእዳ እና ሀብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን እንዲቋቋም በሚኒስትሮች ምክር ቤት ተወስኖ ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነ አስገንዝበዋል።

የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ለሀገር ልማት እና እድገት ላይ የበኩላቸውን አስተዋጽኦም እንዲያበረክቱ መንግሥት የተለያዩ የፖሊሲ ማሻሻያዎች በመቅረፅ እና የአሠራር ሥርዓቶችን በመንደፍ ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

የካቲት 8 ቀን 2013 ዓ.ም የተካሄደው ውይይት በኢትዮጵያ አየር መንገድ እና የኢትዮ-ቴሌኮም የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጻም ግምገማ ላይ ያተኮረ መሆኑን ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።