በአጣየና አካባቢው የፈረሱ ቤቶችን ለመገንባት የሚያግዝ ከ55 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ

ሰኔ 12/2013 (ዋልታ) – የአማራ ደን ኢንተርፕራይዝ በአጣየና አካባቢው በፀጥታ ችግር ምክንያት የፈረሱ መኖሪያ ቤቶችን መልሶ ለመገንባት የሚያግዝ ከ55 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያለው ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን አስታወቀ።

የኢንተርፕራይዙ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ መላኩ ጀምበሬ ድጋፉን ባስረከቡበት ወቅት እንደገለጹት፣ ድጋፉ የተፈናቀሉ ዜጎችን ክረምት ሳይገባ ቤት እንዲያገኙ ለማድረግ የሚደረገውን እቅስቃሴ ለማገዝ ታስቦ የተደረገ ነው።

ኢንተርፕራይዙ በደብረሲና ከተማ አካባቢ በባለቤትነት ከሚያስተዳድረው የደን ሃብት ግምታዊ ዋጋው 55 ነጥብ 1 ሚሊየን ብር የሆነ ለቤት መስሪያ የሚውል የባህር ዛፍ እንጨት ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል ።

በድጋፍ የተበረከተው ፍልጥ እንጨት 13 ሺህ 75 የመኖሪያ ቤቶችን መልሶ ለመገንባት የሚያግዝ መሆኑን አመልክተው፣ ከዚህ በፊትም የእለት ደራሽ ምግብና አልባሳት ድጋፍ ማድረጉንም ነው ያስታወቁት።

በኢንተርፕራይዙ የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘነበ ማንደፍሮ በበኩላቸው፣ ድጋፉ በ30 ሄክታር መሬት ከለማ የባህር ዛፍ ደን ላይ የቀረበ መሆኑን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡