በአፋር ክልል የሉሲ ሙዚየም ሊገነባ ነው

ግንቦት 15/2014 (ዋልታ) በአፋር ክልል ሉሲ ወይም ድንቅነሽ በተገኘችበት “አደአር” አካባቢ የሉሲ ሙዚየም ሊገነባ መሆኑን የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።

ዲያስፖራውን አሳታፊ ያደርጋል የተባለው “ከፈንታሌ እስከ ኤርታአሌ” የቱሪዝም ልማት ፕሮጀክት ወደ ትግበራ ገብቷል።

10ኛው አገር አቀፍ የቱሪዝም ጉባኤ ከትናንት በስቲያ በሰመራ ከተማ የተካሄደ ሲሆን፤ የጉባኤው ተሳታፊዎች ትናንት በክልሉ አፋምቦ ወረዳ የሚገኘዉን የገመሬና ቦሃ ሐይቅ ጎብኝተዋል።

የአፋር ክልል የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አህመድ አብዱልቃድር የሉሲ አጽም በተገኘበት “አደአር” የሉሲ ሙዚየም ግንባታ ለመጀመር የዲዛይን ስራ መጠናቀቁን ገልጸዋል።

የሙዚየሙ ግንባታ በቅርቡ እንደሚጀመርና ለዚሁ ተፈጻሚነት ክልሉ ከቱሪዝም ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ጋር በመሆን በትብብር እየሰራ ነው ብለዋል።

ግንባታው የክልሉን የቱሪስት ፍሰት ለማሳደግና ከዘርፉ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ለመጨመር ያለው አስተዋጽኦ ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።

ክልሉ ከፌደራል መንግስት ጋር በመተባበር “ከፈንታሌ እስከ ኤርታአሌ” የሚል ፕሮጀክት ተቀርጾ አካባቢዎቹን ለጎብኚዎች ምቹ የማድረግ ዲያስፓራውን አሳታፊ ለማድረግ የሚያስችል ስራ መጀመሩንም ነው የገለጹት።

በቅርቡም በአካባቢዎቹም ለሄሌኮፕተር ማረፊያ የሚሆን ጥርጊያ ሜዳ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

በአፋር ክልል አፋምቦ ወረዳ የሚገኘዉን የአዞና ተያያዥ ብዝሃ ሕይወት የሚገኝባቸዉ የገመሬ፣ ቦሃና አቢ ሐይቆችን ለቱሪዝም ልማት ለማዋል አካባቢውን አቋርጦ የሚያልፍ አሳይታ-አፋምቦ-ጂቡቲ ድንበር መንገድ ግንባታ በመጠናቀቁ ለጎብኚዎች ምቹ መሆኑን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ከሰመራ ከተማ 15 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የአለሎበድ ፍልውሃ ለጤና ቱሪዝም ስራ ለማዋል ወደ ፍልውሃው የሚወስድ የጥርጊያ መንገድ በተያዘው ዓመት መሰራቱን ጠቁመዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።

ሉሲ ወይም ድንቅነሽ እንደ አውሮጳዊያኑ የዘመን ቀመር ሕዳር 24 ቀን 1974 በኢትዮጵያ አፋር ክልል “አደአር” በተባለው ቦታ በአሜሪካዊዉ የቅሪተ አካል ተመራማሪ ዶናልድ ጆሃንሰን መገኘቷ ይታወቃል።