በአፋር ጋሌ ኮማ የተፈፀመው የዘር ማጥፋት ተግባር ነው – ወ/ሮ አይሻ ያሲን

ነሃሴ 4/2013(ዋልታ) -በአፋር ክልል ጋሌ ኮማ በአሸባሪው የህወሃት ቡድን የተፈፀመው ግልፅ የዘር ማጥፋት ተግባር ነው ሲሉ የክልሉ ሴቶች ወጣቶችና ህፃናት ቢሮ ሃላፊ  ወ/ሮ አይሻ ያሲን ለዋልታ ገለጹ።

ሀላፊዋ በተለይም ለዋልታ እንደገለፁት፤ አሸባሪው የህወሃት ቡድን ባለፈው ሐሙስ በክልሉ ጋሌኮማ በሚባል አካባቢ በከባድ መሳሪያ የታገዘ ጥቃት በመፈፀም ከ200 በላይ ንፁሃንን ህይወት አጥፍቷል።

ህወሃት በኢትዮጵያ የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት በአሸባሪነት መፈረጁ ይታወሳል።

አሸባሪ ቡድኑ ለሶስት አስርት አመታት ያህል በአምባገነናዊ አመራር ኢትዮጵያን ያስተዳደረ ሲሆን በ1983 ዓ.ም ወደ ስልጣን ከመምጣቱ አስቀድሞ በአማፂነት ይንቀሳቀስ ነበር።

እንደ ወ/ሮ አይሻ ገለፃ የጥቃቱ ሰለባዎች በትምህርት ቤት ውስጥ የተጠለሉ ተፈናቃዮች ናቸው።

የሽብር ቡድኑ በፈፀመው በዚህ የዘር ማጥፋት ጥቃት 200 ንፁሃን ህይወታቸው ማለፉ የተረጋገጠ ሲሆን 48ቱ የደረሱበት አለመታወቁን አስረድተዋል።

ህይወታቸው አልፎ ከተገኙት 200 ንፁሃን መካከልም፤ 107ቱ ህፃናት ሲሆኑ፤ የተቀሩት 32 ሴቶች እና 61 ወንዶች መሆናቸውንም ሃላፊዋ ጠቁመዋል።

የጥቃቱ ሰለባዎች ንፁሃንና በአካባቢው ከተፈጠረው ግጭት ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የሌላቸው ናቸው ያሉት ወ/ሮ አይሻ በመሆኑም ጥቃቱ ግልፅ የዘር ማጥፋት ወንጀል ነው ብለዋል።

በጥቃቱ ጉዳት የደረሰባቸው  ከ30 በላይ ሰዎች ደግሞ በዱብቲ  ሆስፒታል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው እንደሆነም አክለዋል።

በሌላም በኩል አሸባሪው የህወሃት ቡድን ያሎ እና ኡሃ በተሰኙ የክልሉ ሁለት ስፍራዎች ሌላ ጥቃት የመሰንዘር ሙከራ እያደረገ መሆኑን የአፋር ክልል ፕሬዝዳንት ፅ/ቤት ሃላፊ ጎልቤ ሲሌ ለዋልታ ገልጸዋል።\

የሽብር ቡድን በተወሰደበት እርምጃ መዳከሙን ሃላፊው ጠቁመው፤ ከ30 በላይ የቡድኑ ታጣቂዎች የተማረኩ ሲሆን በመቶዎች የሚቆጠሩት ደግሞ መደምሰሳቸውን መሆኑን ተናግረዋል።