ሐምሌ 27/2014 (ዋልታ) የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የሕዝብ፣ ስደተኛና ፍልሰት ጉዳዮች ቢሮ እ.አ.አ በ2022 በኢትዮጵያ ለሚገኙ ስደተኞች ሰብአዊ ድጋፍ የሚውል የ40 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አደረገ።
የቢሮው ምክትል ረዳት ጸሐፊ ኤልዛቤት ካምቤል በአፋር ክልል በሚገኘው ሰርዶ መጠለያ ጣቢያ የሚገኘውን የኤርትራ ስደተኞች ጣቢያ ከተለያዩ አጋር አላት ጋር በመሆን የመስክ ምልከታና ውይይት አድርገዋል።
በጉብኝቱ ወቅት ምክትል ረዳት ጸሐፊዋ እንዳሉት መጠለያ ጣቢያውን ለስደተኞች ምቹ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር የተጀመሩ የመሰረተ ልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።
በተለይም በመጠለያ ጣቢያዉ ለሚገኙ ስደተኞች አስፈላጊዉ የሰብአዊ ድጋፍ፣የምግብና ተያያዥ የሆኑ አቅርቦቶች በበለጠ ትኩረት እንዲደርሱ ከባለድርሻ አካላት ጋር አስፈላጊ የሆኑ ስራዎች እንደሚሰሩ የገለጹት ምክትል ረዳት ጸሃፊዋ እ.አ.አ በ2022 በኢትዮጵያ ለሚገኙ ስደተኞች ሰብአዊ ድጋፍ የሚውል የ40 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ መደረጉን አስታውቀዋል።
በቀጣይም ተቋማቸዉ መሰል ድጋፎችን አጠናክሮ በመቀጠል ከፌዴራልና የክልሉ መንግስት አመራሮች ጋር ተቀራርበዉ እንደሚሰሩ የገለጹ ሲሆን ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆና ስደተኞችን ለማስተናገድ እያሳየች ያለው ቁርጠኝነት የሚደነቅ መሆኑን ምክትል ረዳት ጸሐፊዋ ተናግረዋል።