በኢትዮጵያ ላይ እየተሰነዘሩ ያሉ ያልተገቡ ጫናዎችን ለመመከት እንደሚሰሩ በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ገለጹ

በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን

ግንቦት 23/2013 (ዋልታ) – በኢትዮጵያ ላይ እየተሰነዘሩ ያሉ ያልተገቡ ጫናዎችን ለመመከት እንደሚሰሩ በተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ገልፀዋል፡፡

በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ያተኮረ እና 500 ተሳታፊዎች የተገኙበት “ኢትዮጵያ በአዲስ መንገድ ላይ” የሚል መሪ ቃል የያዘ ውይይት ተካሂዷል፡፡

አምባሳደር ፍጹም አረጋ በውይይቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያ አሁን የገጠሟትን ፈተናዎች ለማክሸፍ በሀገር ውስጥም በውጭም ያለው ኢትዮጵያዊ በተቀናጀ መልኩ እንዲረባረብ ጥሪ አድርገዋል፡፡

የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በበኩላቸው፣ “አሁን ከተለያዩ አቅጣጫዎች የተከፈቱብን ዘመቻዎች በራሳችን አቅም ከምንገነባው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ጋር የሚያያዙ መሆናቸውን ገልጸው፣ ይህን የሀገር አርማ ፕሮጀክት ተባብሮ ማጠናቀቅ ብዙዎችን ጫናዎች እንደሚቀንሳቸው ተናግረዋል፡፡

የግንባታ ሂደቱ 80 በመቶ ለደረሰው የህዳሴ ግድብ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ በመላው አለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ድጋፋቸውን እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

መጪውን ምርጫ በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት የምርጫ ቦርድ የኮሙዩኒኬሽን አማካሪ ወ/ሪት ሲሊያና ሽመልስ ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ቦርዱ ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

አያይዘውም ከአሁን ቀደም ከነበሩት ምርጫዎች በተለየ ቦርዱ ከፍተኛ በጀት ከመንግስትም ከለጋሽ አገራትና ድርጅቶች አግኝቶ ለምርጫው ስኬታማነት እየሰራ ነው ብለዋል፡፡

በምርጫው 200 የግል ተወዳዳሪዎች እንደሚሳተፉብት ገልጸው፣ ይህም ካለፉት ምርጫዎች ልዩ እንደሚያደርገው ተናግረዋል፡፡

በውይይቱ የተሳተፉ የማህበራት አመራሮችና አባላት እንዲሁም ሌሎች ተሳታፊዎችም ከሀገር ውስጥም ከውጭም የኢትዮጵያን አንድነትና ሰላም ለማናጋት እየሰሩ ያሉትንና ያልተገባ ጫና እያደረጉ ያሉትን ኃይሎች ከምን ጊዜውም በላይ እንደሚታገሏቸው ቃል ገብተዋል፡፡

በተለይም የኢትዮጵያን አንድነት ለማስከበር እና እየተሰነዘረ ያለውን ያልተገባ ጫና ለመቋቋም በተደረጃ መልኩ መንቀሳቀስ አስፈላጊ እንደሆነ መግለፃቸውን በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡