በኢትዮጵያ አረንጓዴ ኢኮኖሚን እና የምህድስና ዘርፍን ማሳደግ የኅልውና ጉዳይ ነው- ጠ/ሚ ዐቢይ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ግንቦት 6/2014 (ዋልታ) በኢትዮጵያ አረንጓዴ ኢኮኖሚን እና የምህድስና ዘርፍን ማሳደግ ምርጫ ብቻ ሳይሆን የኅልውና ጉዳይ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይህንን ያሉት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለአፍሪካ ልማት ባንክ ግሩፕ ፕሬዝዳንት አኪንውሚ አዴሲና እና ለጣሊያኑ ሳሊኒ ኩባንያ ሥራ አስኪያጅ ፔትሮ ሳሊኒ የክብር ዶክትሬት በሰጠበት ወቅት ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ንግግር በዛሬው እለት የምናከብራቸው እና እውቅና የምንሰጣቸው ሁለት ሰዎች አረንጓዴ ኢኮኖሚ እና የምህድስና ዘርፎች ባደረጉት ጥረት በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ በጎ ተፅዕኖ በመፍጠራቸው ነው ብለዋል።

የክብር ዶክትሬት ያገኙት አኪንውሚ አዴሲና እና ፔትሮ ሳሊኒ በአኅጉሪቱ በአርዓያነት እንደሚጠቀሱ እምነቴ ነው ሲሉም አክለዋል።

የአረንጓዴ ኢኮኖሚን እና የምህንድስና መስኮች በዓለም ዙሪያ እጅግ የተከበሩ ናቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለብዙ ሀገራትም የጀርባ አጥንት ተደርገው ይወሰዳሉ በማለት ገልፀዋል።

በኢትዮጵያም የአረንጓዴ ኢኮኖሚን እና የምህድስና ዘርፍን ማሳደግ ምርጫ ብቻ ሳይሆን የኅልውና ጉዳይ ነው ብለዋል።

የምግብ ዋስትናን እና ዘላቂ ኢኮኖሚ ለማረጋገጥ አስፈላጊ ዘርፎች ስለመሆናቸው የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የአረንጓዴ ኢኮኖሚና ምህንድስና በአፍሪካ ቀስ በቀስ እያደገ መሆኑን አንስተዋል።

በአኅጉሪቱ የሕዝብ መሰረተ-ልማት እያደገ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢኮኖሚያዊ እድገቱም በቀላሉ ሊወሰድ አይችልም ብለዋል።

በደረሰ አማረ

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW