የካቲት 17/2013 (ዋልታ) – በኢትዮጵያ ከ54 ባላነሱ ቋንቋዎች ሕፃናት አፍ በፈቱበት ቋንቋ እየተማሩ ይገኛሉ ተባለ፡፡
ይህም የተገለፀው በሰመራ ሲካሄድ በቆየው 11ኛው “በአፍ መፍቻ ቋንቋ የመናገር ቀን” መርሐግብር ማጠናቀቂያ ላይ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የዘንድሮው ዓለም አቀፍ በአፍ መፍቻ ቋንቋ የመናገር ቀን በዓል በአፋር ሰመራ ሲከበር በክልሉ የባህል ቡድን በተለያዩ የመድረክ ዝግጅቶች ስነ ስርዓቱን ማድመቁም ተጠቁሟል፡፡
በበዓሉ መክፈቻ ላይ የክልሉ አፌ-ጉባኤ ወይዘሮ አሚናት ሴኮ እና የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮው ኃላፊ አቶ አሊ መሃመድ ጉርባኢስ ተገኝተዋል፡፡
በመርሐግብሩ ላይ ከስምንት ያለነሱ ጥናታዊ ጽሑፎች ከዩኒቨርሲቲዎች የተጋበዙ ምሁራን ቀርበው ገለፃና ውይይቶች ተደርጎባቸዋል፡፡
በዋናነት በቋንቋ የመማር ማስተማር ሂደት ውስጥ በአዲሱ የስርዓተ-ትምህርት ስርዓት አማካይነት በየአካባቢው የሚካሄዱ የመማር ማስተማር ሂደቶች ቋንቋዎቻችን የማበልጸግ፣ የማልማትና የመጠበቅ ሥራዎች ተጠናክሮ እንዲቀጥሉ የሚመለከታቸው አካላት ኃላፊነታቸውን ወስደው ያለ ምንም የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሙያዊ ሥራዎች እንዲሰሩ ውይይቶች መካሄዳቸው ነው የተጠቀሰው፡፡
በሙያዊ ስነምግባር እንዲያከናወኑ ማበረታታት እንደሚገባ በማሳሰብና ነፃ ሀሳቦች የተንፀባረቁበት መሆኑም ተገልጿል፡፡
በመጨረሻም የበዓሉ ተሳታፊዎች የአፋር ባህል ማዕከል ሙዚየምን በመጎብኘት መርሐግብሩ መጠናቀቁን ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡