በኢትዮጵያ የህገ መንግሥትና ፌዴራሊዝም እሳቤዎች እንዲሰርፁ ለማድረግ በትኩረት መስራት ይገባል – አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር

ግንቦት 8/2014 (ዋልታ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከፍትህ አካላት ጋር በህገ መንግሥቱ አተረጓጎም እና አፈፃፀም ላይ በሚስተዋሉ ችግሮች ላይ ትኩረት ያደረገ ምክክር እያካሄደ ነው፡፡

በመድረኩ የተገኙት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በኢትዮጵያ ውስጥ የዴሞክራሲ ባህል እንዲጎለብት፣ ዘላቂ ሰላምና ፀጥታ እንዲሰፍን እንዲሁም በዜጎች ዘንድ የህገ መንግሥትና ፌዴራሊዝም እሳቤዎች እንዲሰርፁ ለማድረግ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

አፈ ጉባኤው አክለውም በህገ መንግሥቱ ትርጉም ላይ ግንዛቤ ለማሳደግ እንዲሁም ምክር ቤቱ ባሳለፋቸው ህገ መንግሥታዊ ውሳኔዎችና አፈፃፀም ላይ በመመካከር የህግ መንግሥት የበላይነትና ህገ መንግሥታዊነትን ማረጋገጥ ቀዳሚ ተግባር ማድረግ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

በመድረኩ በህገ መንግሥት ትርጉም ፅንሰ ሃሳብ ላይ ያተኮረ ጥናታዊ ጽሑፍ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ወንድማገኝ ታደሰ (ዶ/ር) ቀርቧል፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ 104 የህገ መንግሥት ትርጉም ያስፈልጋቸዋል የተባሉ ጉዳዮች ከህገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ለምክር ቤቱ መቅረባቸው ተገልጿል፡፡

ከነዚህም 90 በመቶ የሚሆኑ ጉዳዮች ምክር ቤቱ የህገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤን የውሳኔ ሀሳብ በመቀበል ማፅደቁ የተነገረ ሲሆን 10 በመቶ የሚሆኑትን ባለመቀበል የህግ መንግሥት ትርጉም አያስፈልግም በማለት ውሳኔ ሰጥቷል ተብሏል፡፡

የህገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ የህገ መንግሥት ትርጉም አያስፈልጋቸውም ተብለው በተሰጠው ውሳኔ ቅር በመሰኘት ለምክር ቤቱ የቀረቡ የህገ መንግሥት ትርጉም ይግባኞች ከ600 በላይ መሆናቸውም የተነገረ ሲሆን ከነዚህ ዉስጥ 2 መዝገቦች የህግ መንግሥት ትርጉም ያስፈልጋቸዋል የሚል ውሳኔ ተሰጥቶባቸዋል ተብሏል፡፡

በመድረኩ የምክር ቤቱ የፍትህ አካላት፣ የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ አባላት እና ባለድርሻ አካላት  ተገኝተዋል፡፡

በአመለወርቅ መኳንንት