በኢትዮጵያ የንግዱ ዘርፍ ላይ ሙስና እና ብልሹ አሰራር እየተባባሰ መምጣቱ ተጠቆመ

መጋቢት 12/2014 (ዋልታ) በኢትዮጵያ የንግዱ ዘርፍ ላይ ሙስና እና ብልሹ አሰራር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ ”የንግድ ዘርፍ አገልግሎት አሰጣጥ ማነቆ የወለደው ሙስና እና ብልሹ አሰራር” በሚል መሪ ሃሳብ ከተለያዩ የዘርፉ ተዋናዮች ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡

በመድረኩ በዚሁ ዙሪያ የቀረበው የውይይት መነሻ ፅሑፍ በኢትዮጵያ የንግድ ዘርፍ ላይ ሙስና እና ብልሹ አሰራር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱን አመላክቷል።

ለችግሩ መባባስም በፖለቲካው፣ በማኅበራዊ እና በኢኮኖሚው የሚስተዋሉ የግልጽነትና የአሰራር ብልሹነት ችግር እንዲሁም የተቋማዊ አሰራር ግድፈቶች መሆኑ ተገልጿል።

የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ- ሙስና ኮሚሽነር ሳሙኤል ኡርቃቶ (ዶ/ር) ከንግዱ ዘርፍ ጋር የተያያዙ ብልሹና ህገ ወጥ የአሰራር ችግሮችን ለመፍታት የተቀናጀ ጥረት የሚጠይቅ መሆኑን ገልጸዋል።

የዛሬው ውይይትም የችግሩን ስፋትና ውስብስብነት በመገንዘብ የጋራ መፍትሄ ለማበጀት የተካሄደ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ የንግድ ዘርፍ ላይ ሙስና እና ብልሹ አሰራር አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን የተናገሩት ኮሚሽነሩ በዚህ ወንጀል ውስጥ የሚሳተፉትን በጥንቃቄ በመለየት የህግ ተጠያቂ የማድረግ ሥራ ይከናወናል ብለዋል።

የድሬዳዋ ንግድ ፅሕፈት ቤት ኃላፊ አሚኑ ጠሃ የግብይት እንቃስቃሴዎች ውስጥ ያለውን ማነቆ ለመፍታት ሁላችንም መታገል ይኖርብናል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የአዲስ አበባ ነጋዴዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት ዘሀራ መሀመድ በበኩላቸው የንግድ ብልሽቱ ሁላችንንም የሚጎዳ በመሆኑ ህጋዊና ፍትሃዊ የንግድ ሰንሰለት እንዲኖር በጋራ መስራት አለብን ብለዋል።