በኢትዮጵያ የኢንዶኔዥያ አምባሳደር የተመራ ልዑክ ለስራ ጉብኝት አርባ ምንጭ ገባ

መስከረም 28/2014 (ዋልታ) በኢትዮጵያ የኢንዶኔዥያ አምባሳደር አል ባስይራ ባስኑር የተመራ ልዑክ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት አርባ ምንጭ ገባ፡፡

ለልዑኩ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ዘዉዴን ጨምሮ ከፍተኛ አመራሮች አቀባበል አድርገዋል፡፡

የጉብኝቱ ዋና ዓላማ የቢዝነስ ቱ ቢዝነስ ግንኙነት ለመፍጠር እና የኢንቨስትመንት አማራጮችን በመለየት የኢንዶኔዥያ ባለሀብቶች በዞኑ በተለያዩ የስራ ዘርፎች እንዲሰማሩ ለማድረግ ነው ተብሏል፡፡

አምባሳደሩ በተፈጥሮ ወደታደለችው አርባምንጭ ከተማ በመምጣታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀው፣ አከባቢው በጣም ውብ ከመሆኑ ባሻገር ለም አፈር ያለዉ በመሆኑ ለተለያዩ ኢንቨስትመንቶች ምቹ አከባቢ ነው ብለዋል፡፡

በአምባሳደሩ የተመራው ልኡክ በሚኖረው ቆይታ ከጋሞ ዞን አስተዳደር እና ከአርባምንጭ ከተማ ንግድ ማህበራት ዘርፍ ምክር ቤት ጋር ውይይት ያደርጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከዞኑ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡