በኢትዮጵያ የኬሚካል ኢንዱስትሪ ፓርክ ለማቋቋም እንቅስቃሴ ተጀመረ

በኢትዮጵያ የኬሚካል ማምረቻ  ኢንዱስትሪ ፓርክ ለማቋቋም እንቅስቃሴ መጀመሩ ተገለጸ፡፡

የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዮት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢ/ር ደዬሳ ለታ፣ ዘርፉ ለኢንዱስትሪው የጀርባ አጥንት በመሆኑ ሁሉን  ኢንዱስትሪዎች  መመገብ የሚችል የኬሚካል ማምረቻ ለማቋቋም እንቅስቃሴ መጀመሩን  አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኬሚካል ውጤቶች አምራቾች ዘርፍ ማህበር ባካሄደው አመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ሀገሪቷ ከዘርፉ መጠቀም የሚገባትን ጥቅም ማግኘት እንድትችል በሚታዩ ክፍተቶች ላይ ትኩረት ተደርጎ ሊሰራባቸው እንደሚገባ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ኬሚካል ውጤቶች አምራቾች ዘርፍ ማህበር ሰብሳቢ አቶ በቀለ ፀጋዬ የዘርፉን ችግሮች መቅረፍ እንደሚገባ ገልጸው፤ በተለይም ከውጭ ምንዛሪ፣ ፋይናንስና ብድር፣ ኤል ሲ አገልግሎት ክፍያ፣ የመሬት አቅርቦት፣ የኤሌክትሪክ ኃይል አለማግኘት እና ከጉምሩክ አሰራሮች ጋር ያሉ ሰፊ ክፍተቶች ትኩረት ሊደረግባቸው ይገባል ብለዋል፡፡

በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የብረታ ብረትና ኬሚካል ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዮሃንስ ድንቃየሁ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ ከግብርና መር ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመሸጋገር በምታደርገው ጥረት ዘርፉ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡

ማህበሩ የ2012 በጀት አመት ክንውን ሪፖርትና የ2013 ዓ.ም እቅድ ላይ ውይይት እና የመተዳደሪያ ደንብ ማሻሻያ አድርጓል፡፡

(በህይወት አክሊሉ)