በኤሌክትሪክ የሚሰራ አውሮፕላን የመጀመሪያውን በረራ አደረገ

በኤሌክትሪክ የሚሰራ አውሮፕላን

መስከረም 18/2015 (ዋልታ) የእስራኤሉ ኢቪዬሽን ኩባንያ በኤሌክትሪክ የሚሰራ አውሮፕላኑን ለስምንት ደቂቃ በአየር ላይ ማብረሩ ተገለጸ፡፡

የእስራኤሉ ኢቪዬሽን ኤርክራፍት የተሰኘው ኩባንያ ሙሉ ለሙሉ በኤሌክትሪክ የሚሰራ አውሮፕላን የመጀመሪያውን በረራ በማድረግ ከአሜሪካው ዋሽንግተን ኤርፖርት በመነሳት በ3 ሺሕ 500 ጫማ ከፍታ ሁለት አብራሪዎች እና ሰባት ተሳፋሪዎችን በመያዝ የሙከራ በረራውን እንዳካሄደ ሲኤንኤን ዘግቧል።

የኩባንያው ስራ አስኪያጅ ግሪጎሪ ዳቪስ እንዳሉት በአውሮፕላን የሞተር ኃይል ታሪክ ከ1950ዎቹ በኋላ ሲለወጥ እንዳላዩ ገልጸው ላለፉት 70 ዓመታት ታሪክ ውስጥ ሁሉም አውሮፕላኖች በነዳጅ የሚንቀሳቀሱ እንደነበሩ አስታውሰዋል፡፡

በአሁኑ ሙከራ ሙሉ ለሙሉ በኤሌክትሪክ የሚሰራ አውሮፕላን ለማምረት የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ እንደሆነም አክለዋል።

የዚህን አውሮፕላን የባትሪ ቴክኖሎጂ ልክ በኤሌክትሪክ ቻርጅ ከሚሰሩት ተሽከርካሪዎች ጋር ተመሳሳይ ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነም ተገልጿል።

የአንድ አውሮፕላን ቻርጅ የማድረጊያ ጊዜን በ30 ደቂቃ ውስጥ ለማድረግ ታቅዷል የተባለ ሲሆን የአውሮፕላኑን አሁናዊ ፍጥነት በሰዓት 287 ማይል ርቀት ይጓዛልም ተብሏል።

በፈረንጆቹ 2015 ላይ የተቋቋመው ኢቪዬሽን ኩባንያ ከአራት ዓመት በኋላ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ አውሮፕላኖችን ለዓለም ገበያ የማቅረብ እቅድ አስቀምጦ ነበር። ይሁንና የኮሮና ቫይረስ እና ሌሎች የዓለም ክስተቶች በተቀመጠው ጊዜ የኤሌክትሪክ አውሮፕላኖችን አምርቶ ወደ ዓለም ገበያ ማድረስ እንዳልተቻለ ተገልጿል።

የአሜሪካ የአቪዬሽን ቁጥጥር ባለስልጣን በኤሌክትሪክ የሚሰሩ አውሮፕላኖቹን የጥራት ደረጃ እንዲገመግም እና እንዲመረቱ ፈቃድ እንዲሰጥ የማድረግ ስራው በቅርቡ እንደሚጀምርም ተቋም አስታውቋል።

ይህ አውሮፕላን የሙከራ በረራውን በስኬት አጠናቋል የተባለ ሲሆን በረራውን ጨርሶ ወደ ምድር ለማረፍ ግን የተወሰኑ ችግሮች አጋጥመዋል ተብሏል።

ከአንድ ዓመት በፊት የሙከራ በረራውን የማጠናቀቅ እቅድ የነበረው ይህ የአቪዬሽን ተቋም በመጥፎ የአየር ንብረት እና ኮሮና ቫይረስ ምክንያቶች ስራውን ባሰበው ጊዜ መከወን እንዳልቻለ ጠቁሟል።

በቀጣይ አንድ ዓመት ውስጥ የሙከራ ጊዜውን በማጠናቀቅ በአሜሪካ ባሉ ግዛቶች መካከል የአገልግሎት መስጠት ሙከራዎችን እንደሚያከናውንም አስታውቋል።

በእቃ ማጓጓዝ ስራ ዘርፍ የተሰማሩ ንግድ ድርጅቶች ከወዲሁ የኤሌክትሪክ አውሮፕላኖችን ለመግዛት ፍላጎት አሳይተዋል የተባለ ሲሆን ዲኤችኤል፣ ግሎባልኤክስ እና ሌሎችም ተቋማት ፍላጎት ካሳዩ ድርጅቶች መካከል ዋነኞቹ ናቸው መባሉን የአልዐይን መረጃ አመላክቷል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW
ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth
ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured
ቲዊተር https://twitter.com/walta_info
አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!