በአዲስ አበባ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችና ሕገወጥ ሰነዶች ከነተጠርጣሪዎቻቸው ተያዙ

ከቤተ መንግሥት የጠፉ ቅርሶች

ኅዳር 23/2014 (ዋልታ) በአዲስ አበባ ከተማ ከሽብርተኛው ሕወሓት ጋር ግንኙነት ያላቸውንና ሌሎች ሕገወጦችን በሕግ ቁጥጥር ስር ለማዋል እየተወሰደ ባለው እርምጃ አሁንም በርካታ ሕገወጥ መሳሪያዎችና የተለያዩ ሰነዶች እየተያዙ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በደረሰው ጥቆማ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 ኤድናሞል ህንፃ ስር በሚገኝ በአንድ ግለሰብ መጋዘን ውስጥ ባደረገው ድንገተኛ ፍተሻ 21 የሬዲዮ መገናኛዎች፣ በቤተ መንግሥት ብቻ የሚገኝ አንድ ጋሻ፣ አንድ ክላሽንኮቭ መሳሪያ ከ30 መሰል ጥይቶች ጋር በቁጥጥር ስር እንዲውል ተደርጓል።

በተመሳሳይ በዚሁ በቦሌ ክፍለከተማ ወረዳ 3 አትላስ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሌላ አንድ ግለሰብ መኖሪያ ቤት ውስጥ በተደረገ ፍተሻ አንድ ሽጉጥ ከመሰል ጥይቶች ጋር በቁጥጥር ስር መዋሉን ለመረጃው ቅርበት ያላቸው ታማኝ ምንጮቻችን አረጋግጠዋል፡፡

በተጨማሪም በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ቀበሌ 19 በአንድ ግለሰብ መኖሪያ ቤት ውሰጥ የፀጥታ አካላት ባደረጉት ፍተሻ በሕገ ወጥ መንገድ የተዘጋጁ 18 የኢትዮጵያ ፓስፖርቶች፣ 3 የልደት ካርዶች፣ 13 የሥራ ልምዶች፣ 10 የህክምና ማስረጃዎች፣ 22 የወሳኝ ኩነት መሸኛዎች፣ 6 የተለያዩ የባንክ ደብተሮች፣ 7 የተለያዩ የቀበሌ መታወቂያዎች፣ አንድ ካሜራ፣ 4 ማህተም እና አንድ የከበረ ድንጋይ የተገኘ ሲሆን ግለሰቡም በቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጉን ለዋልታ የደረሱት መረጃዎች ይጠቁማሉ።