በኤጀንሲው የሀዋሳ ማዕከል በአፍሪካ ደራጃ አሸናፊ መሆኑ ለመንግስት መስሪያ ቤቶች ትምህርት የሚሰጥ ነው- ዶክተር ሊያ ታደሰ

ዶክተር ሊያ ታደሰ

ነሐሴ 25/2013 (ዋልታ) – በኢትዮጵያ የመድሃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ የሀዋሳ ማዕከል በካይዘን አተገባበር በአፍሪካ ደራጃ አሸናፊ መሆኑ ለሁሉም የመንግስት መስሪያ ቤቶች ትምህርት የሚሰጥ መሆኑን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ፡፡

የጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ የስራ አመራሮች በሀዋሳ በመገኘት የቅርንጫፉን የስራ እንቅስቃሴ ጎብኝተዋል፡፡

በኤጀንሲው ስር በሀገር አቀፍ ደረጃ 18 ቅርንጫፎች እንዳሉ በመጥቀስ የሀዋሳው ማዕከል በካይዘን አተገባበርም ሆነ በስራ አፈጻጸሙ ከቀዳሚዎች ተርታ መገኘቱን ሚኒስተሯ ገልጸዋል፡፡

የጤና ሚኒስትሯ የመድሃኒት ብክነትን ለመቀነስና ቀልጣፋ አገልግሎትን ለተጠቃሚዎች ለመስጠት የካይዘን ፍልስፍና አዎንታዊ ሚና ያለው በመሆኑ ዋናውን መስሪያ ቤትን ጨምሮ ሌሎች መስሪያ ቤቶችንም ከሀዋሳው ቅርንጫፍ ትምህርት ሊቀስሙ ይገባል ብለዋል፡፡

በኤጀንሲው የሀዋሳ ቅርንጫፍ ዋና ስራ አስኪያጅና የደቡብ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ዘመን በየነ ቅርንጫፉ ኢትዮጵያ በመወከል በአፍሪካ ደረጃ አሸናፊ በመሆኑ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸው በቀጣይም የስራ ጥራትና ቀልጣፋ አገልግሎትን ለመስጠት ያነሳሳናል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ በአውሮፓውያኑ 2030 በአፍሪካ ቀዳሚ መድሃኒት አቅራቢ ተቋም ለመሆን እያደረገ ላለው ጥረት ሽልማቱ መነሳሻ በመሆን እንደሚያገለግል በመጥቀስ በተጠናቀቀው የ2013 በጀት አመት 2.4 ቢሊየን ብር የሚገመት መድሃኒት ወደ ተጠቃሚዎች መሰራጨቱንም ማስረዳታቸውን የደሬቴድ ዘገባ ያመለክታል፡