በእስራኤል የሚኖሩ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ አባላት ለመልሶ ግንባታ ሥራ ጀመሩ

ታኅሣሥ 24/2014 (ዋልታ) በእስራኤል የሚኖሩ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ አባላት በኢትዮጵያ የመልሶ ግንባታና ማቋቋም ሂደት ተሳትፎ ማድረግ የሚያስችል ሥራ መጀመራቸውን የእስራኤል ፓርላማ (ክኔሴት) የቀድሞ አባል ሽሎሞ ሞላ ገለፁ።
መንግሥት አሸባሪው ትሕነግ በአማራና አፋር ክልሎች ወረራ በፈጸመበት ወቅት ያደረሰውን ውድመት መልሶ ለማቋቋም ያቀረበውን ጥሪ በመቀበል ድጋፍ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ለኢዜአ ገልጸዋል።
በእስራኤል የሚገኙ ዲያስፖራዎች በተለይም የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት ውድመት በደረሰባቸው አካባቢዎች መዋዕለ ነዋያቸውን በማፍሰስ ምጣኔሃብቱን እንዲያነቃቁ ቅስቀሳ እየተደረገ ስለመሆኑ ጠቅሰው፤ በዚህም የታየውም ፍላጎት አበረታች የሚባል እንደሆነ ተናግረዋል።
ሐኪሞች፣ መኃንዲሶችና በተለያዩ መስኮች የተሰማሩ ባለሙያዎች በሙያቸው ኢትዮጵያን ማገዝ ይፈልጋሉ ያሉም ሲሆን መንግሥትም ባለሙያዎቹ አገራቸውን የሚያገለግሉበት አሰራር እንዲዘረጋ ጠይቀዋል