በኦሮሚያ በድርቅ ለተጎዱ አርሶ አደሮች ድጋፍ ተደረገ

ሚያዝያ 26/2014 (ዋልታ) የኦሮሚያ ወጣቶች አደረጃጀት ቢሮ በክልሉ በድርቅ ለተጎዱ  አርሶ አደሮች ከ17 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የስንዴ ምርጥ ዘር ድጋፍ አደረገ።
ቢሮው በክልሉ በድርቅ ለተጎዱ 7 ዞኖች ነው ድጋፍ ያደረገው።
አደረጃጀቱ በአጠቃላይ ከ 17 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት 3 ሺሕ 442 ኩንታል የስንዴ ምረጥ ዘር ከክልሉ ወጣቶች በማሰባሰብ ድጋፍ መደረጉ ተጠቁሟል።
የድጋፉ ዋና አለማ በድረቅ የተጎዱ አርሶ አደሮች የምርጥ ዘር እጥረት እንዳያጋጥማቸው እና ወጣቱ የመረዳዳት አንዲሁም የመተጋገዝ ባህልን እንዲያጎለብት መሆኑም ነው የተገለፀው።
በድጋፍ ርክክብ ሥነ ሥርዓቱ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል የግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ጌቱ ገመቹ የኦሮሚያ ወጣቶች ቢሮ አደረጃጀት የክልሉ ወጣቶችን በማስተባበር ለግብርና ሥራ ያደረገውን ድጋፍ ያደነቁ ሲሆን ቢሮው በክልሉ በድርቅ ለተጎዱ ዞኖች የእርሻ ግብአትን እያቀረበ መሆኑንም ተናግረዋል።
በዚህም ከ15 ሺሕ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር በድርቅ ለተጎዱ አከባቢዎች በነፃ ለአርሶ አደሩ መሰጠቱን ጠቅሰዋል።
በድጋፍ ርክክቡ የኦሮሚያ ክልል የግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ጌቱ ገመቹ ፣ የዞን ተወካዮች እና የክልሉ የወጣቶች አደረጃጀት ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በእመቤት ንጉሴ
ለፈጣን መረጃዎች፦
ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth
አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!