በኦሮሚያ ክልል ከ13 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት የመስኖ ግድቦች ግንባታ እየተካሄደ ነው

የካቲት 26/2014 (ዋልታ) በኦሮሚያ ክልል ግብርናውን ከዝናብ ጠባቂነት ለማላቀቅ ከ13 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት መካከለኛና አነስተኛ የመስኖ ግድቦች ግንባታ እየተካሄደ መሆኑ ተገለጸ።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊስ አማካሪ አምባሳደር ግርማ ብሩ፣ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር)፣ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) እና የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ ዛሬ በምስራቅ ሸዋ ዞን ሊበን ጭቋላና ወንጂ ኩሩፍቱ በበጋ መስኖ የለማውን የስንዴ ማሳ ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ ወቅት ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ እንደገለጹት ለበጋ መስኖ ልማት 20 ሺሕ የሚጠጉ ከፍተኛ ጉልበት ያላቸውና መካከለኛ የውሃ መሳቢያ ሞተሮች ለአርሶ አደሮች ተከፋፍለዋል።

በክልሉ ሁሉም ዞኖች ከ355 ሺሕ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ ስንዴ በመስኖ እያለማን ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ተጨማሪ 270 ሺሕ ሄክታር መሬት ለዘር ዝግጁ እየተደረገ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

በሚቀጥለው ዓመት አንድ ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት ዕቅድ መያዙን ጠቁመው ለዚህም የመስኖ ግድቦች ግንባታና የጥልቅ የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ግብርናውን ከዝናብ ጠባቂነት ለማላቀቅ ከ13 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ወጪ መካከለኛና አነስተኛ የመስኖ ልማት ግድቦችን እየገነባን ነው ብለዋል።

በዚህም በቀጣይ አራት ዓመታት የክልሉን ግብርና ከዝናብ ጠባቂነት በማላቀቅ በመስኖ የሚለማው መሬት እስከ 4 ሚሊዮን ሄክታር ለማድረስ ግብ ተቀምጦ እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) በበኩላቸው በኦሮሚያ ክልል በግብርና ሴክተር እየተመዘገበ ያለው ውጤት ተስፋ ሰጪ እንደሆነና በክልሉ በመስኖ እየለማ ያለው ስንዴ በሁሉም ክልሎች በማስፋፋት ከውጭ የሚገባውን ምርት በአገር ውስጥ መተካት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

በተለይ አርሶ አደሩ የውሃ መሳቢያ ሞተር፣ የመካናይዜሽን አገልግሎትና የገበያ ትስስር ተደራሽ ለማድረግ የገጠር ፋይናንስ አሰራር እየዘረጋን ነው ብለዋል።

በምስራቅ፣ ደቡብ ምዕራብና ምዕራብ ሸዋ ዞኖች የመስኖ ስንዴ ልማት በተሻለ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ መመልከታቸውን የተናገሩት ደግሞ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) ናቸው።

አርሶ አደሩ በኩታ ገጠም ስንዴን በተሻለ ሁኔታ እያለማ መሆኑንና አገሪቱ በምግብ ራስዋን እንድትችል በተለይ በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችል ተግባር ነው ብለዋል።

ለአርሶ አደሩ የገበያ ትስስር በመፍጠር የልፋቱን ዋጋ እንዲያገኝ መደረግ እንዳለበትም መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊስ አማካሪ አምባሳደር ግርማ ብሩ አርሶ አደሩ ያለበትን የውሃ እጥረት ለመፍታት አምራቹን ያሳተፈ የጥልቅ ጉድጓድ ቁፋሮ፣ አነስተኛና መካክለኛ ግድቦች ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመዋል።

በተጨማሪም የገጠር ፋይናንስ ተደራሽነትን ማረጋገጥ በቀጣይ የሚሰራበት መሆኑንም አመልክተዋል።