በኦሮሞ ስም የሚነግድው የኦሮሞ ጠላት ሸኔ

ነሐሴ 26/2013 (ዋልታ) – ሸኔ የሽብር ቡድን በኦሮሞ ስም የሚነግድ ትናንት የኦሮሞን ሲገድል ከነበረው የሕወሓት የሸብር ቡድን ጋር ጋብቻ የፈጸመ የኦሮሞ ጠላት ነው ሲሉ አባ ገዳ ሁንዴ በየነ ገለጹ።

የኦሮሞ ወጣት ከመከላከያ ሰራዊት ጎን በመቆም የኢትዮጵያን ኅልውና ማስጠበቅ እንዳለበትም አሳስበዋል።

አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ለአገር የሚራራ አንጀት የሌለው፣ በእናቶች እንባ የሚደሰት እና አገር ስትደማ የሚረካ የከሃዲዎች ስብስብ መሆኑን ነው አባ ገዳ ሁንዴ የገለጹት፡፡

የሽብር ቡድኑ በሥልጣን በቆየባቸው ዓመታት ዜጎችን ለእልቂት፣ አገርን ለምጣኔ ሃብታዊ መሽመድመድ፣ ወንድማማች የሆኑ የኢትዮጵያን ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦችን ለቅራኔና ግጭት ለመዳረግ ሴራ ዘርግቶ ሲሰራ መቆየቱ ደግሞ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው ብለዋል።

የሽብር ቡድኑ በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ በታላቅ ክብርና ደስታ በሚከበረው የኢሬቻ ክብረ በዓል ላይ የፈጸመው የዜጎች እልቂት የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።

ሽብርተኛው የሕወሓት ቡድን ዜጎች ለመብታቸው አደባባይ ሲወጡ ምላሹ አፈ-ሙዝ፣ ሃሴቱ ደግሞ የህዝብ ዋይታ መሆኑም እንዲሁ።

ትላንት የኦሮሞን ሕዝብ ሲጨፈጭፉ የነበሩት የሸኔና የወያኔ የሽብር ቡድኖች ዛሬ በጋራ እንደሚሰሩ ይፋ ማድረጋቸው አዲስ ጉዳይ አለመሆኑንና የሽብር ቡድኖቹ የኦሮሞ ሕዝብ ጠላት መሆናቸውን ያረጋገጠ መሆኑን ተናግረዋል።

የሸኔ የሽብር ቡድንም በኦሮሞ ስም የሚነግድ ትናንት ኦሮሞን ሲገድል ከነበረ ቡድን ጋር ጋብቻ የፈጸመ ለኦሮሞ የማይበጅ የጥፋት ኃይል መሆኑን አንስተዋል።

የኦሮሞ ወጣት መስዋትነት የከፈለላትን ኢትዮጵያ ከሃገር መከላከያ ሠራዊት ጎን በመቆም ለህልውናዋ መዋደቅ እንዳለበትም አባ ገዳ ሁንዴ በየነ ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።